በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
የተከበራችሁ አንባቢዎቻችን ፤ በቀደሙት ክፍሎች በየርዕሱ የዳሰስናቸው አስጨናቂ ፣ አስገራሚ ፣ አስደንጋጭና አሳሳቢ
እውነታዎች ፤ ብዙዎችን ባለማመንና ግራ መጋባት ውዥምብር ውስጥ ሊከቱ ይችላሉ:: እዚህ ላይ ታዲያ ፤ አላማችን አንባቢን ለማስደንገጥ
፤ አልያም አለም ልትጠፋ ነው ሰማይ ሊወድቅ ነው በሚል ጩኸት ተስፋ
ለማስቆረጥ አይደለም:: የዘመኑን እውነተኛ ገፅታ በአግባቡ ተረድቶ ራሱን ፣ ቤተሰቡን ብሎም ሀገሩን ለመታደግ ፤ በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀስ
ለማነሳሳት እንጂ:: መልካም ህልም ውስጥ ተደብቆ ከመኖር ምን ህልሙ ቢጣፍጥ ንጋት አስከፊውን እውነታ በግድ ይዞ መምጣቱ አይቀርምና
በጊዜ ነቅቶ የቀን ቅዠትን መፋለም ሐላፊነት የሚሰማው ክርስቲያንና ሀገር ተረካቢ ዜጋ ድርሻና ግዴታ ነውና::
ይህ ጥናታዊ ዘገባ ፤ የችግሩ ቅንጫቢ እንጂ ፤ የተዘፈቅንበትን አዘቅት ጥልቀትም ሆነ ሁለንተናዊ ገፅታ የሚያሳይ ዘገባ
አይደለም:: በቀደሙት ክፍሎች የተመለከትናቸው አሃዛዊ መረጃዎችም የጉዳዩን አሳሳቢነት ለማሳየት በቂ ቢሆኑም ፤ ማኅበረሰባችንን
አቆራኝተው ስለያዙት ባህላዊ ፣ ሃይማኖታዊና ፤ ግብረ ገባዊ እሴቶች መሸርሸር ፤ ይህንንም ተከትሎ እየደረሰብን ያለውን ሁለንተናዊ
መፈረካከስ ፤ ሁለገብ በሆነ መልኩ ለማሳየት ረዥም ጊዜና ፤ ጥልቅ የሆነ ጥናት ያስፈልጋል።
አንዳንዶች … የተቀረው አለም በባህል ፣ በስነ ምግባርና ፤ በሃይማኖት ዘርፎች ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ቢገባም ፤ ሀገራችን
በአንጻራዊነት የተሻለ ደረጃ ላይ መገኘቷን በመጥቀስ ሊዘናጉና ሌሎቻችንንም
ሊያዘናጉን ይሞክራሉ ፤ የተቀረውን አለም ያሰጠመው ባህር እስከ አንገታችን
እንደዋጠን ባለማስተዋል ፤ መተንፈስ መቻላችንን ብቻ በመጥቀስ ማንቀላፋትን ይሻሉ:: አርቀው በማሰብ ጎረቤቶቻችንን የፈጀው እሳት
፤ ነገ ወደኛ መምጣቱ አይቀሬ እንደሆነ ሊመለከቱ ፤ ነግ በኔም ብለው ከእንቅልፋቸው ሊነቁ እንደሚገባቸው አልተረዱም። እናም እነዚህ
ወገኖች ‘አሜሪካና የምእራቡ አለም ስለተዘፈቁበት ችግር እኔ ምን አገባኝ?’ ይላሉ ፤ እኛ ግን በሀገርኛ አባባል ‘ጎረቤትህ ሲታማ
ለኔ ብለህ ስማ’ እንላቸዋለን።
እውነት ለመናገር እንደ ደሴት ፤ በአካባቢያችን ካሉ እንግዳ
ተፅዕኖዎች ተጠብቀን የምንኖርበት ዘመን የማብቃቱ ጉዳይ ፤ ለብዙዎች የተገለጠ አይደለም:: ሀቁ ግን ‘መንደር ሆናለች አለማችን’
የሚለውን ብሂል በሬዲዮ ከማድመጥ አልፈን በተጨባጭ ለውጡን ማስተዋል ከጀመርን ሰንበትበት ማለታችን ነው። የግሎባላይዜሽን ሰደድ እሳት የሀገሮችን መለያ ማንነት እየበላ ቃጠሎው ባስነሳው
ጭስም ሌላውን እየሸፈነና እያመሳሰለ በፍጥነት በመጋለብ ላይ ሲሆን ፤ ገና ወላፈኑ ያልነካቸው ሀገራት በቁጥር አጅግ ጥቂቶች ናቸው::
ሀገራት እና ሕዝቦች ከሌሎች የተለዩ የሚያደርጓቸውን ባህላዊ እሴቶች ፣ የአኗኗር ዘይቤዎችና ፤ የማንነት አሻራዎች በፍጥነት እያጡ ፤ መገለጫቸው የሆኑ ቀለማትም
በግዙፉ የግሎባላይዜሽን ማሰሮ ውስጥ እየቀለጡ ወደ ወጥነት ግራጫና ሕይወት አልባ ወደሆነ መመሳሰል እየተለወጡ ይገኛሉ::
ከዚህም
በላይ ኢትዮጵያ ሀገራችን በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎቻቸው ፤ በመላው አለም ተበትነውባቸው ከሚገኙ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗ ፤
የዚህ የግሎባላይዜሽን ሰደድ እሳት ገፈት ቀማሽ በመሆንም ቀዳሚነቱን ከያዙት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል::
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ፤ ከተበተኑት የዳያስፖራ ማሕበረሰብ መካከል በርካታዎቹ የሚገኙት አመጻ ፣ ሃይማኖት አልባነትና
፤ የስነ ምግባር እሴቶች መንኮታኮት በከፍተኛ ሁኔታ በነገሰባቸው
በአሜሪካና በምዕራብ አውሮፓ መሆኑ ጉዳቱን ያብሰዋል:: እዚህ ላይ
ታዲያ ፤ መረሳት የሌለበት አብይ ነጥብ ፤ በሌሎች ታዳጊ ሀገራት ላይም እንደሚስተዋለው የዳያስፖራው ማሕበረሰብ የሀገሪቱ የፋይናንስ
፣ የፖለቲካና የባህል አሰላለፍ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድር አካል መሆኑ ነው:: ከውጪ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ ስናስብ
፤ በሐዋላ ከሚላከው ገንዘብ ጋራ ፤ አብሮ የሚገባውንና የብዙ አባወራዎችን በር የሚያንኳኳውን ደባል ተፅዕኖ ለመረዳት ጠቢብ መሆን
ግድ አይልም::
ከዚህ
ሁሉ ጋር በሆሊዉድ በይፋ ከተመረቁ ፤ ሳምንት እንኳ ያልሞላቸውን ፊልሞች ፤ ለሀገር ቤት ተመልካቾች ለእይታ የሚያበቁ ሳተናዎቹ
ሲኒማ ቤቶቻችን ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ ከተሞች የተለበሱ ፋሽን ልብሶችን አድነው ለሀገር ቤት ደምበኞች የሚያቀርቡ ፤ ከተሞቻችንን
ያጨናነቁ ቡቲክ ቤቶቻችንና ፤ ከልጅ እስከ አዋቂ ፤ ረጅም ሰዓታትን በኮምፒውተር መስኮት ላይ አፍጥጦ እንዲውል ፤ ግድ እያለ ያለውን
የፌስቡክ አዲክሽን ፤ ግምት ውስጥ ስናስገባ ‘ባዕድ ከሆኑ የባህል ፣ የኢኮኖሚና ፤ የፖለቲካ ተፅዕኖ ነጻ የሆነችዋ ኢትዮጵያ’
፤ ያከተመላት መሆኑን እንገነዘባለን ፤ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ማዶ ፤ በአሜሪካና መሰሎቿ ፤ ለሚፈጸሙ ጉዳዮችም ግድ ሊኖረን እንደሚገባ
ወደ ማመን እንመጣለን።
እናስ?
ምን ብናደርግ ይበጃል? ሁሉም እያደረገ እንዳለው ፤ በመክነፍ ላይ ያለው ፈጣን የእድገትና የስልጣኔ ባቡር ሳያመልጠን እንንጠላጠልበት
ይሆን? ወይስ በአብረቅራቂ መጠቅለያ ታሽጎ የቀረበልንን ስጦታ አይረባንም ብለን እንግፋው ይሆን? ግን ደግሞ እንደ መቃብር ከላይ
ተለስኖ ያማረ ፤ ውስጡ ግን በሚከረፋና በሚቀፍ በድን የታጨቀ ስጦታ እንደሆነስ? እውን እየተጓዝንበት ያለነው የምዕራቡ ጎዳና ወደ
ስልጣኔ የሚያደርሰን ትክክለኛው መንገድ ነውን? ብዙዎች ሊሉ እንደሚችሉትስ ከቀረበልን ጥቅል ውስጥ ፤ ጠቃሚ የሚባለውን ፤ ለኢኮኖሚ
እድገት የሚያበቃንንና ፤ ሆዳችንን እንድንሞላና እንድናጌጥ የሚያስችለንን ጥበብ ወስደን ፤ አጥፊውን ፤ ለስነ ምግባር ብልሹነትና
እምነት አልባነት የሚዳርገውን እሳቤ መጣል እንችል ይሆን? ባልተጠበቀ መልኩስ እነዚህ ሲታዩ ለየቅል የሚመስሉ አማራጮች የአንድ
ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ቢሆኑ? የአንዱ የስጦታ ጥቅል መንታ ፍሬዎች የሆኑስ እንደሁ? የምዕራቡ የስልጣኔ ባቡርስ ቢመርጡት ባህላዊ
፤ ማኅበራዊና ፤ ሃይማኖታዊ ዝቅጠትን እንደማሕበረሰብ የሚያስከፍል
፤ የተከለከለው የእውቀት ፍሬ አምሳል ቢሆንስ? ፤
የተከበራችሁ አንባቢዎቻችን ፤ ይህ ጥናታዊ ዘገባ እኒህን መሰል ወሳኝ ጥያቄዎች ለመመለስ በቂ አለመሆኑ እርግጥ ነው
፤ ያም ሆኖ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ ፤ ጊዜ አይሰጤ የሆኑ በርካታ ጥያቄዎች ፤ ቁርጥ ውሳኔያችንንም የሚሹ አያሌ
ጉዳዮች ፤ በፊታችን እንደተጋረጡ በማሳየት ረገድ ፋይዳው የሚያጠያይቅ አይሆንም።
‘ምንተ ንግበር’ን በአዕምሯችን እያመላለስን
እስኪ አንድ አፍታ ምናልባትም ከላይ ላነሳናቸው ጥያቄዎች መልስ ሊሰጠን ወደሚችል ተጨባጭ ጉዳይ እንመለስ ለመሆኑ እንዲህ ወዳለ
አለም አቀፋዊ የማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ቀውስ ውስጥ እንዴት ልንገባ ቻልን? ተፈጥሯዊ በሆነ የእርስ በርስ መስተጋብር በአጋጣሚ ወይስ
በሌላ በተጠና ስውር ተንኮል?
በርግጥ
ከልጅነታችን አንስቶ በየትምህርት ቤቶቻችን መምህራኖቻችን እየነገሩን ያደግነው የመጀመሪያውን ነው። ከዚህም የተነሳ የአለም ታሪክ
፤ በየዘመኑ በሚነሱና ትውልድ በዘፈቀደ በሚያደርጋቸው ግንኙነቶች መነሾነት በሚፈጠሩ ክስተቶች የተሞላ ፤ ፍጹም ባልታቀደ ጎዳና
የሚሄድ ተፈጥሯዊ ሂደት እንደሆነ ብናምን አያስገርምም።
ሂስቶሪሲዝም በአለም ታሪክ ውስጥ የተመዘገቡ ክንዋኔዎችና ክስተቶች ሙሉ ሳይንሳዊ ትንታኔ ሊሰጥባቸው የሚችሉ እንደሆኑ
በማቅረብ ከታሪክ መጋረጃ በስተጀርባ ፤ በጥቂቶች የሚፈጸሙ ደባዎች ፣ ሴራዎችና ፣ ዱለታዎች እንደሌሉ ያስቀምጣል። በገናና እና
አለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው ዩኒቨርስቲዎች የከተሙ ሊቃውንትም የሚያረጋግጡልን ነገር ቢኖር ይህ የታሪክ ትንታኔ መነጽር የማይጠረጠር
ሐቅ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን እውን እነሱ እንደሚሉት ይህ አተያይ የማያሻማ ነውን፡፡
በቅርብ አስርት አመታት የተጠራቀሙ በርካታ የታሪክ
መረጃዎች በኢፋዊው የታሪክ ዘገባ ሊመለሱ የማይችሉ እንቆቅልሾችን አንግበው ለታሪክ ሊቃውንቱ ራስ ምታት ሆነዋል ፡፡ እኒህ ሊቃውንት
እንዲሁም ከነሱ ጀርባ የቆሙት ኢንተርናሽናል ዩኒቨርስቲዎችና የመገናኛ ብዙሃን ግን ለነዚህ ፊታቸው ለተጋረጡና መፍትሄ ለሚያሻቸው
እንቆቅልሾች መፍትሄ ከማፈላለግና መረጃዎቹን ያገናዘበ የታሪክ ምስል ከማጠናቀር ይልቅ ለመረጃዎቹ ጀርባቸውን መስጠት አሊያም ጭፍን
በሆነ ሁኔታ ማጣጣልን መርጠዋል፡፡
ሳይንስ
ሁሉን ተጨባጭ መረጃ ግምት ውስጥ ያስገባ፣ ከግል ዝንባሌና አመክንዮ የጸዳ ታሪካዊ ምስል እንዲነደፍ ግድ ይላል፡፡ ለተጨባጭነታቸው
ምንም አሻሚነት የሌላቸውን እኒህ መረጃዎች ግምት ውስጥ ለማስገባት ለፈቀደና ከእውነተኛ የሳይንስ ተመራማሪ የሚጠበቀውን ቆራጥነት
ተሞልቶ መረጃዎቹ ወደሚያደርሱት እልባት እስከመጨረሻው ለመገስገስ ለቆረጠ የታሪክ ተንታኝ የነኚህ እንቆቅልሾች መልስ የማያሻማ ነው
ይኸውም አዲሶቹን መረጃዎች ግምት ውስጥ ያስገባ ግን ደግሞ እስከዛሬ የተማርናቸውን የታሪክ ‘እውነታዎች ’ እንዳልነበሩ የሚያደርግ
አዲስና ስር ነቀል የታሪክ ግንዛቤ ለመቀበል መዘጋጀት ነው፡፡ ነገር ግን በዚህች ለሐቅ የቆሙ ፋኖዎች ብቻ ሊጓዙባት በሚፈቅዷት
ጠባቢቱ መንገድ ለመጓዝ ግዙፋኑ የታሪክ ምርምር ማእከላትና በውስጣቸው ያሉ የታሪክ ጠበብት ማቅማማታቸው በብብታቸው የደበቁትን የተለየ
አጀንዳ ያሳብቅባቸዋል፡፡
ከ20ኛው
መ.ክ.ዘ መገባደጃ አንስቶ በርካታ አዳዲስ የታሪክ መረጃዎች በብዙሃኑ ሕብረተሰብ እጅ ሊገቡ በቁ፤ ምክንያቱ የመረጃ አቢዮት መምጣትና
በቀደሙ ዘመናት ፈጽሞ ያልታየ የግንኙነት እና የመረጃ መረብ መፈጠር ነበር፡፡ ከ40 ዓመታት አስቀድሞ ድንገት ብቅ ያለው የኢንተርኔት
የመረጃ መለዋወጫ ዘዴ ከእነዚህ አመታት በፊት ፈጽሞ ሊታሰብ በማይችል ሁኔታ ከተጽእኖ የጸዳና ሳንሱር ያልተደረገ ቀድሞ በጥቂቶች
እጅ ብቻ ተገድቦ የቆየ ጥሬ መረጃ በሕብረተሰቡ እጅ እንዲገባ በር ከፍቷል፡፡ ይህም ክስተት ያለንበትን ትውልድ ከርሱ ቀድሞ ከነበረው ከየትኛውም ትውልድ ሁሉ በተሻለ
ሁኔታ ያልተበረዘ፣ ያልተከለሰ፣ እውነተኛ የታሪክ ምስል ለማግኘት በሚያስችል ልዩ የግንዛቤ ማማ ላይ እንዲቆም አስችሎታል፡፡ ቀድሞ
በጥቂቶች እጅ ባሉ ካዝናዎችና መደርደሪያዎች ከሕዝብ እይታ ርቀው የነበሩ የግል ታሪኮች፣ የምስጢር መልእክታት፣ ያልታተሙ መጻሕፍት፣
በኮንግረስ ተጽእኖ ለሕዝብ ይፋ የተደረጉ ምስጢራዊ የደህንነት መረጃዎች እንዲሁም የውስጥ አዋቂ ምሁራን ምስክርነቶች ተደማምረው
የከሰቱት ምስል በማያሻማ አኳኋን ይፋዊው የታሪክ ዘገባ የተሳሳተ ከመሆንም አልፎ ‹ድል አድራጊዎች ታሪክን አንዳሻቸው ይጽፉታል›
የሚለውን የፈረንጆች ተረት እውነተኝነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ሆኗል፡፡
የአዲሶቹን
መረጃዎች ለሕዝብ እይታ መብቃትን ተከትሎም ወሳኝ የታሪክ ክስተቶች የሆኑ እንደ የቦልሼቪክ አብዮት አጀማመር፣ የጃፓን የፐርል ሐርበር
ጥቃት፣ የኒክሰን የወተርጌት ቅሌት፣ የሉሲታንያ መርከብ መስጠምና ሌሎች መሰል በርካታ የታሪክ ክስተቶችን እንደአዲስ በመፈተሽ የጠራ
ታሪካዊ እልባቶችን የያዘ አዲስ የታሪክ ንቅናቄ ብቅ አለ፡፡
የዚህ የታሪክ ክለሳ እንቅስቃሴ ፈር ቀዳጆች የሆኑ በርካታ ምሁራን ያለፉት አራት መቶ አመታት ታሪክ ለዘመናት ከመጋረጃው
በስተጀርባ ተሸሽገው በረቀቀ ሁኔታ ግባቸውን ለማሳካት በሚጥሩ ስውር ማሕበራት የተሸረበ ሴራና ሆን ተብሎ የታቀደ የሸፍጥ ትረካ
መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ለማሳየት በቅተዋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ማስታወሻ፡- “ቴክኖሎጅ ያዘመነው የእኛ ትውልድና ፤ ሚዲያ መራሹ ማኅበራዊ ምስቅልቅል” በሚል ርዕስ በአምስት
ተከታታይ ክፍሎች ያቀረብንላችሁ ይህ ጥናታዊ ጽሑፍ ፤ በቅርቡ ለእይታ የሚበቃውና በዝግጅት ላይ የሚገኘው “የመጨረሻው መጀመሪያ”
የተሰኘ ዶኪመንታሪ የመጀመሪያ ክፍል ስክሪፕት ነው፡፡