Pages

Thursday, March 27, 2014

ቴክኖሎጂ ያዘመነው የእኛ ትውልድና ፤ ሚዲያ መራሹ ማሕበራዊ ምስቅልቅል Part 4

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡



ከቅርብ አመታት ወዲህ የሲኒማ ቤቶችንና ፤ በየሳሎኖቻችን ያሉ የቴሌቪዥን መስኮቶችን እያጨናነቁ የመጡት ፤ እንደ ሃሪ ፖተር ፣  ዘ ሎርድ ኦፍ ዘ ሪንግስ ፣  ዘ ቫምፓየር ዳያሪስ ፣  ሄል ቦይ ፣  ሼርሎክ ሆልምስ ፣  የመሰሉ ፊልሞች ፤  ከልጅ እስከ አዋቂ  ትውልዱ  በአፍቅሮተ አስማት ወጥንቆላ እንዲለከፍ ፤ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ::


ፊልሞቹ  ከገፀ-ባህሪያት አመራረጣቸው አንስቶ ፤ መልከ ግቡ በሆኑና ግርማ ሞገስን በተላበሱ  ተወዳጅ የስክሪን ከዋክብት የሚተወኑ ፤ በታሪክ አወቃቀራቸው ለተመልካች ስሜቶች ቅርብ በሆኑ የተሰናሰሉ ታሪኮችና የተመጠኑ ቀልብ ሳቢ ግጭቶች የተሰካኩ ፤ በዝግጅታቸውም ከድምፅ አጠቃቀም እስከ አልባሳት መረጣ ፤ ከመብራት አጠቃቀም እስከ ቀለማት ምጣኔ ድረስ ፤ ምንም የሚጎረብጥ ነገር እንዳይኖራቸው ተደርገው ከመሰራታቸው የተነሳ ተመልካች የሚገልጧቸውን የጨልማ ኃይላት አሰራር ፤ ያለ አንዳች ማቅማማት እንዲቀበል ፤ እንዲያም ሲል በዕለት ተዕለት ኑሮው ተግባራዊ ሊያደርጋቸው እንዲናፍቅ የሚገፋፋ አንዳች ኃይል አላቸው።





ቅጥ ያጡ የጭካኔ ድርጊቶች ፣ ደም ማፋሰስና ፣ እልቂት መገለጫቸው የሆኑ ፊልሞች 24 ሰአት ሳሎኖቻችንን ሲያወኩና እርቃናቸውን በሚታዩ ሴቶች የተጨናነቁ ፤ ዝሙት ቀስቃሽ የሙዚቃ ቪዲዮዎች ፤ የህጻናቶቻችንን አእምሮ ሲያጨቀዩ ማየትም የተለመደ ሆኗል:: 


በአሜሪካ ብቻ ሰይጣናዊ መልዕክታትን የሚሰብኩና ፤ ለጨለማ ኃይላትበተለይም ለዲያቢሎስ ፤ አምልኮ እንደሚገባ በይፋ የሚያውጁ ብላክ ሜታል የተሰኙ በአስርት የሚቆጠሩ ታዋቂ የሮክ ሙዚቃ ቡድኖች ይገኛሉ:: 

ባጠቃላይ የ21ኛው መ.ክ.ዘ. መባቻ ፤ ይህን ትውልድ በከፍተኛ ፍጥነትና ለማመን በሚያዳግት ግን ደግሞ ተጨባጭነቱ በማይካድ ሁኔታ የጨለማ ኃይላት ምርኮኛ በማድረግ ላይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም::

ለበርካታ ወራት የፊልም ሽያጭ ሰንጠረዡን ተቆጣጥሮ የቆየው ፤ የሃሪ ፖተር ተከታታይ ፊልም ፤ በገበያ ላይ ካስመዘገበው እጅግ አስደማሚ ስኬት አንስቶ ፤ አንቶን ላቬይ በሳን-ፍራንሲስኮ በይፋ እስከከፈተው የሰይጣን ቤተ-አምልኮ ድረስ በግልጽ እንደተስተዋለው ፤ በተለይ የምዕራቡ አለም ከእለት ወደ እለት ይበልጥ በሰይጣናዊ ተፅዕኖ ስር እየወደቀ ሲሆን ፤ በጥንቆላና በሌሎች የጨለማ ግብራት ውስጥ የሚዘፈቀው የሕብረተሰብ ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሻቀብ ላይ ይገኛል።

በመካከለኛው ዘመን ፤ በአስማትና በጥንቆላ ተግባር የተሰማሩ ግለሰቦችን ለመለየት ብሎም በሕግ ለመቅጣት ሲባል ፤ ማለስ ማልፊካረም የተሰኘ የሕግ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ስራ ላይ እንደዋለ ታሪክ ምስክር ነው ፤ ማለስ ማልፊካረም በዚህ በእኛ ዘመን ‘ከባድ ግፍ’ እንደነበረ ይነገራል ፤ አስማትና ጥንቆላም ፌዝና ተራ ተረት ተረት ተደርገው ይቆጠራሉ ፤ እንዲያም ሆኖ ፤ በመፃሕፍት ፤ በሙዚቃዎችና ፤ በፊልሞች ህጻናት ሳይቀሩ እንዲማሯቸው ብዙ ድካም ይደከማል ፤ … ለምን?

 

ከሁለት አስርት አመታት በፊት በአውሮፓ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ፤ በታላቋ ብሪታንያ ብቻ … እስከ 100 000 የሚደርሱ … ጠንቋዮችና ሰይጣንን የሚያመልኩ ግለሰቦች ይገኛሉ ፤ በጀርመን ደግሞ 10 000 ሰዎች ፤ የተለያዩ አይነት የጥንቆላ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ ታውቋል::

በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የሕግ አስፈጻሚ አካላት ፤ መቃብራትን ከማፈራረስ አንስቶ ፤ ህጻናትን ዝሙት አነሳሽ ለሆኑ ፊልሞችና የሕትመት ውጤቶች እስከ መጠቀም ፣ ሰዎችን ገድሎ መስዋዕት አድርጎ ማቅረብ ፣ የሰው ስጋ መብላት ፣ አስገድዶ ግብረ ሰዶም መፈጸም ፣ እንስሳትን መቆራረጥ ፣ አብያተ ክርስቲያናትን ማርከስ ድረስ ፤ በሚጎርፉላቸው የወንጀል ሪፖርቶች በመጥለቅለቅ ላይ ናቸው:: 


በአሁኑ ወቅት ፤ በአብዛሃኛዎቹ የምዕራብ ሀገራት የሚገኙ ታዳጊ ተማሪዎች ፤ የመማሪያ ደብተሮቻቸው ፤ በሰይጣናዊ ምስሎችና ምልክቶች ፣ ቁልቁል ተዘቅዝቀው በተሳሉ መስቀሎች ፣ የሰይጣን አምልኮ ምልክት በሆኑ ባለአምስት እግር ኮከቦችና ፤ የአውሬው ቁጥር በመባል በሚታወቀው 666 ቁጥር የደመቁ ፤ የሚለብሷቸው ዘመናዊ አልባሳት ፤ የአጋንንትና የሰዎች የራስ ቅል የተሳሉባቸው ፣ የሚያደምጧቸውም ሙዚቀኞች ፤ በዘፈኖቻቸውና ባሳተሟቸው አልበሞች ሽፋን አምልኮተ ሰይጣንን የሚሰብኩ ናቸው::


ለዚህ ከየአቅጣጫው ለሚረጭ ሰይጣናዊ አስተምህሮ ፤ ጆሯቸውን ከሚሰጡ ታዳጊዎች በርካታዎቹ ፤ ቀስ በቀስ ሰዎችን መስዋዕት ወደ ማድረግ ፤ ራስን ወደ ማጥፋትና ፤ መሰል አሰቃቂና አስጸያፊ የሆኑ ድርጊቶችን ወደ መፈጸም ያደርሳቸዋል:: እስኪ የሰይጣን አምልኮ አሻራ ካረፈባቸው ታዋቂ የወንጀል ድርጊቶች መካከል ፤ ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን እንመልከት፡፡ 

  
ጆሴፍ ቤንሰንና ኤድዋርድ ቤኔት ይባላሉ ፤ የ18 እና የ19 ዓመት ታዳጊዎች ናቸው። የሰይጣን አምልኮ ስርዓት እየፈጸሙ በነበሩበት ወቅት ፤ እንስሳትን ለመስዋዕትነት ቆራርጠዋል ፤ የገዛ ራሳቸውን ደም አፍስሰዋል ፤ በዚህም ሳይበቃቸው ፤ ያዳቆነ ሰይጣን እንዲሉ የ18 ዓመቷን ወጣት ፤ ሚሼል ሙርን ገድለዋታል::


በኦክላሆማ የሞት ፍርድ ከተፈረደባቸው መካከል ፤ በእድሜ ትንሹ የሆነው የ17 ዓመቱ ሱተን ሴላስ ፤ እናቱንና የእንጀራ አባቱን እጅግ አሰቃቂ በሆነ አኳኋን ገድሏቸዋል ምክንያቱ ደግሞ እያከናወነው የነበረውን የሰይጣን አምልኮ ስርዓት ሊያስቆሙት በመሞከራቸው ነበር::


የ17 ዓመቱ ስኮት ዋተርሃውስ ፤ ለዲያቢሎስ መስዋዕት ለማቅረብ በማሰብ ፤ የ12 ዓመቷን ታዳጊ አፍኖ ከወሰዳትና ካሰቃያት በኋላ ገድሏታል::



ፒት ሮውላንድ ይባላል ፤ የ17 ዓመት ታዳጊ ነው ፤ ከሌሎች ሦስት ታዳጊ ባልንጀሮቹ ጋር በመሆን የሰይጣን አምልኮ የሚፈጽም ማኅበር ያቋቁማል ፤ ከዚያም ድመትን ለመስዋዕት ካቀረቡ በኋላ ፤ ደም ሲያሰክራቸው ወደገዛ ጓደኛቸው ስቲቭ ኒውበሪ በመዞር ፤ በቤዝቦል መጫወቻ ዱላ ቀጥቅጠው ገድለውታል ስቲቭን በሚቀጠቅጡበት ወቅት ለሰይጣን የቀረበ መስዋዕት ነው!! እያሉ ደጋግመው ይጮሁ ነበር:: 


ሪቻርድ ራሚሬዝ ፤ 13 ሰዎችን በመግደሉና ሌሎች 30 ወንጀሎችን በመፈጸሙ ምክንያት ፤ በ1980ዎቹ የሚዲያን ትኩረት የሳበ ወንጀለኛ ነበር ፤ በ1985 ክረምት ብቻ በርካታ ሰለባዎቹን ሌሊት እያደባ በማፈን ቀጥቅጦ ፣ አስገድዶ በመድፈር ፣ ከቆራረጣቸው በኋላ ዘግናኝ በሆነ አኳኋን ጥይት በማርከፍከፍ ገድሏቸዋል::



በ1989 በጋ ላይ በአሜሪካና ሜክሲኮ ድምበር በምትገኘው ማታሞራስ ፤ የ13 ሰዎች አስከሬን ተቆራርጦና አንድ ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ ተገኘ ፤ ተቆፍረው ከወጡት አስክሬኖች መካከል አንድ የ16 ዓመት ወጣት ሬሳ ይገኝበታል:: ይህን አሰቃቂ ድርጊት የፈጸመው ሰይጣንን የሚያመልኩ የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎች የመሰረቱት አንድ ቡድን ነበር:: የዚህ ቡድን አባላት አዘውትረው በሚያከናውኗቸው አስፈሪና አሰቃቂ የጥንቆላ ስርዓታት ወቅት ሰዎችን መስዋዕት አድርጎ ማቅረብ ከጠላቶቻቸው እጅ እንደሚያድናቸውና አስማታዊ ከለላን እንደሚያሰጣቸው ያምኑ ነበር::  ከሰለባዎቻቸው መካከል  በመዶሻ የተቀጠቀጡ ፣ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ የተቆራረጡና አንጎላቸው ፣ ልባቸው እና ሌላ የሰውነት ክፍላቸው ተወስዶ በደም እንዲቀቀል የተደረጉ ይገኙባቸዋል::

የተከበራችሁ አንባቢዎቻችን … በድብቅ ይከናወኑ የነበሩ የርኩሰትና የጥንቆላ ተግባራት ፤ አለ አንዳች ሃፍረት በይፋ የሚፈጸሙበት ፤ የሰይጣን ጀሌዎችም በገሀድ አባላቶቻቸውንና ግብረ አበሮቻቸውን መመልመል የጀመሩበት ጊዜ መጥቷል:: በምዕራቡ አለም ፤ ሕቡዕ የጥንቆላ ቡድኖች ፤ በሕዝብ ማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ ርኩሰቶችንና የሰይጣን አምልኮ መገለጫ ምስሎችን በመሳል በሕብረተሰቡ ላይ የማይጠፋ የጽልመት ጠባሳን ማሳደር ከጀመሩ ሰነባብተዋል::



በዘመናችን ፤ በተለይ በሰለጠነው የአለም ክፍል የሰይጣን አምልኮና ነገረ አጋንንት  እንዲያንሰራራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ግለሰቦች መካከል ፤ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ፤ ታዋቂው እንግሊዛዊ አሌይስተር ክሮውሊ ነው። ክሮውሊ የአሁኑ ትውልድ እንደአርአያ ከሚቆጥራቸው ስመ ጥር ግለሰቦች በርካታዎቹን ደቀ መዝሙር ለማድረግ የቻለ የተሳካለት መምህር የነበረ ሲሆን ፤ ማጂክ በተሰኘው መጽሐፉ አንድን ህጻን በተሳካ ሁኔታ እንዴት መስዋዕት ማድረግ እንደሚቻል በዝርዝር የገለጸ የለየለት የዲያቢሎስ ጉዳይ አስፈጻሚ ነው፡፡



የክሮውሊ የተፅዕኖ አሻራ ፤ እንደ ኦርዶ ቴምፕሊ ኦርየንቲስ ፣ ኮሎኔል ሚካኤል አኲኖ እንደመሰረተው ቴምፕል ኦፍ ሴት  ፣ እንደቢትልስ የሮክ ሙዚቃ ቡድንና ፤ ዊል ስሚዝና ቶም ክሩዝን የመሰሉ ዝነኛ ግለሰቦች አባል እንደሆኑበት ቸርች ኦፍ ሳይንቶሎጂ ፤ ባሉ ቡድኖች ላይ በጉልሕ ይታያል::


እ.ኤ.አ በ1966 ዓ.ም አንቶን ላቬይ በሳን-ፍራንሲስኮ የመሰረተውና በአንድ ወቅት እስከ 10 000 የሚደርሱ ተከታዮችን አፍርቶ የነበረው የሰይጣን ቤተ-አምልኮ ፤ ሌላው የዚህን ትውልድ ደረጃ የሚገልፅ ሁነኛ ማሳያ ነው:: አንቶን ላቬይ ፤ በተለምዶ ‘የሰይጣን መጽሐፍ ቅዱስ’ … Satanic Bible … እየተባለ የሚጠራውን መጽሐፍና ፤ የሰይጣን መሳቢያ ስርዓታትን ደርሶ ለሕትመት ያበቃ ሲሆን ፤ ይኸው ‘የሰይጣን መጽሐፍ ቅዱስ’ በቅርቡ በአማርኛ ተተርጉሞ በሕቡዕ በመሸጥ ላይ ይገኛል:: አስገራሚው ነገር ፤ መጽሐፉ በአሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕትመት በበቃበት ወቅት ፤ በመላው ሀገሪቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ በሁለት እጥፍ ለመሸጥ በቅቶ የነበረና በአንዳንድ የኮሌጅ ካምፓሶች ደግሞ አስር እጥፍ የተሸጠ መሆኑ ነው::  


ይቆየን ... 


ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር።
 
 

 
 

No comments:

Post a Comment