Pages

Monday, May 11, 2015

እውነቱን እውነት ፤ ሀሰቱንም ሀሰት ማለት ይገባል!! መቻቻልና መገናዘብም ፤ መበራረዝና መቀላቀል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
እውነቱን እውነት ፤ ሀሰቱንም ሀሰት ማለት ይገባል!!

መቻቻልና መገናዘብም ፤ መበራረዝና መቀላቀል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡


ጤና ይስጥልን …


ይህችን አጭር ማስታወሻ (አስተያየት) ለመጻፍ ያነሳሳን ጉዳይ …. ከሰሞኑ ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን በክርስቲያን ወንድሞቻችን ላይ የተፈጸመውን አረመኔያዊ የግድያ ተግባር ተከትሎ ፤ በሰማዕታቱ ማንነት ላይ (ይልቁንም … ቀድሞ “ጀማል” ፤ አዲስ በተገኘው መረጃ ደግሞ “ኤፍሬም” ስለተባለ ወገናችን ማንነት) ፤ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ያየነው ቅጥ ያጣ የሃሳብ (የአመለካከት) ልዩነት (ሽኩቻ) … ነው፡፡ … የቀደመው ወይንስ አዲሱ መረጃ ይሻላል የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር ብዙም ሊባልበት የሚችል ባይሆንም ቅሉ ፤ በተያያዥነት ያየናቸው ሊታለፉ የማይገባቸው ጉዶዮች አሉና ፤ የመረጃውን ጉዳይ እንደ መንደርደሪያ አድርገን ወደ ጉዳያችን እንዘልቃለን፡፡


ከሁሉ በፊት … በሃይማኖታቸው ምክንያት ሰማዕትነት የተቀበሉትን ወንድሞቻችንን አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱሳንን ባከበረበት ክብር ያከብራቸው ፤ ለቅዱሳን ሰማዕታትም ያቀዳጃቸውን የክብር አክሊል ያቀዳጃቸው ፤ ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ያጽናናቸው ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን፡፡


ይህ አሰቃቂ መርዶ ከተሰማባት ከዚያች ክፉ ዕለት እንጀምር … ዜናውን የያዘው የምስል ወድምፅ ውጤት ከአሸባሪ ቡድኑ መለቀቁን ተከትሎ የተለያዩ የዜና አውታሮች ወሬውን እየዘግቡትና … የተለያዩ የውጭ መንግስታትም በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ጭካኔ እያወገዙ ባሉበት ሰዓት … መንግስታችን … “የድርጊቱ ሰለባዎች ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውንግብፅ የሚገኘው ኢምባሲ አላረጋገጠም ፣ በርግጥ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ለማረጋገጥ እየጣርን ነው” … ማለቱን ሰምተን ፤ ብዙዎቻችን … “የሟቾቹን አስከሬን አግኝቶ ማረጋገጥ በማይቻልበት ሁኔታ … ምን ነካቸው? … ደግሞስ እኛ የወገኖቻችንን መልክና የፊት ገፅታ አጣነውን? … ቢሳሳቱስ … “ወገኖቻችን ታረዱ” ብለው በማዘናቸውና በመቆጨታቸው … የሚያባጭባቸው ማን ሊኖር?” … የሚሉና ፤ መሰል መሪር ሀዘን ወለድ ሃሳቦችን … መለዋወጣችን ይታወቃል፡፡


ከላይ መንግስትን በወቀስንበት አመክንዮ መሰረትነት … በወንድማችን ኤፍሬም ማንነት ላይ እየተንጸባረቀ ያለውን ልዩነት ለመረዳት እንሞክር ፤ … መንግስት ዜናውን ከሰማበት ቅጽበት አንስቶ መሠዋታቸውን እውቅና ቢሰጠውና አስከትሎም ተገቢ የሚባሉ እርምጃዎችን ቢወስድ ፤ ከዛም የድርጊቱ ገፈት ቀማሾች ኢትዮጵያውያን አለመሆናቸው ቢረጋገጥ ምን ይከሰት ነበር? … እንደ ብዙዎቻችን እምነት … ምንም … እንዲያውም መንግስት ለሕዝብ ያለውን ወገንተኝነት ያሳየበት ክስተት ሆኖ ያልፋል … ወዲህ ደግሞ እንመለስ … አስቀድሞ  “ጀማልየተባለ ሙስሊም ወንድማችን በሊቢያ ከተሠዉ ክርስቲያኖች ጋር አብሮ ተሠዉቷል” ተባለ … ይህምየኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ፍቅር ማሳያ” ተደርጎ ተወሰደ …  በ “‹ጀማል› አምሳልም አንዱ ለሌላው ያለውን ተቆርቋሪነት አየን” አልን … ሁሉም ጥሩ ነው … አንዳችም ችግር የለበትም … በቅርቡ ደግሞ ፤ “የተለያዩ ሁኔታዎች የፈጠሩት የመረጃ ክፍተት እንጅ … ‹ጀማልነው ተብሎ ሲነገርለት የነበረው ወንድማችንኤፍሬም የተባለ ኤርትራዊ ፤ ቃኘው ሠፈር ይኖር የነበረ ክርስቲያን ነው” የሚል አዲስ መረጃ መጣ … ቀጥሎ ሊሆን የሚገባው ነገር የመረጃውን ትክክለኝነት ማጣራት ነው ፤ … ይህ ከሆነ በሁዋላ ታዲያ ፤ የቀደመውን እንደተቀበልን ሁሉ ይህንን የማንቀበልበት ምን ምክንያት ይኖራል? … በምን ሒሳብ አዲሱ መረጃ (እውነቱ) የቀደመ ፍቅራችንን የሚቀማን ተደርጎ ይቆጠራል? … እንደምንስ እንደ አንድ ሀገር ሕዝብነት ያስተሳሰረንን ገመድ እንደሚያላላ ተደርጎ ይወሰዳል? … እንዲህ ከሆነስ ታዲያ ፤ ከላይ መንግስት ቢሳሳት

እን ወገንተኛነቱን አሳየ እንጅ ሌላ ነገር የለውም (ምንም አይባልም) ፤ ስንል የነበረው ነገር እርግጥ እንዲያ አድርጎ ተሳስቶ ቢሆን ኖሮ አይሰራም ነበር ማለት ነው?



የቀድሞውን … የሀሰት ማንነትና ታሪክ የሚሹ ወገኖች ለዚህ ፍላጎታቸው የተለያዩ ምክንያቶችን እንደሚያቀርቡ ሁሉ ፤ በሌላ በኩል የአዲሱን (የትክክለኛውን) መረጃ መነገርንም የሚደግፉት እንደ አመክንዮ የተለያዩ ምክንያቶችን ያመጣሉ (ከቤተሰቡ ፤ ከቤተክርስቲያን ፤ …. አንጻር) … እውነት ለመናገር ግን የአንድን መረጃ ጠቀሜታ አልያም ጉዳት መተንተን የሚቻለው የመረጃውን ምንነት ካወቁ በሁዋላ ነው … ስለሆነም በኛ አመለካከት መረጃው መነገር የሚኖርበት እውነት ስለሆነ ብቻና ብቻ ነው! … ከዚያ በ|ላ ቋሚ ብዙ ያወራልና … ነገርን እንደ መረዳታችን መጠን … እንደ እምነታችን … እንደ አመለካከታችን … እንደ |ላ ታሪካችን … እንደምንከተለው ርዕዮት … የፈለጋችሁትን ስም ልትሰጡት ትችላላችሁ … እንደፈለግን ልንተረጉመውና ልንበልተው እንችላለን፡፡ … በድጋሚ ግን እነ እንቶኔም ደስ እንዲላቸው … እነንትናም እንዳይከፋቸው ሳይሆን … እውነት ስለሆነ ብቻ እውነቱ መነገር ይኖርበታል፡፡


ለአብነት … ይህንኑ የሀሳብ ልውውጥ አስመልክቶ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ፤ የአዲሱን (የትክክለኛውን) መረጃ ይፋ መሆን በመቃወም … “ለሰብዓዊነት የተከፈለን መስዋዕትነት ዝቅ አድርጎ ለሃይማኖት የተከፈለ አድርጎ አቀረበብኝ” ማለታቸውን እናንሳ … አመለካከታቸውን እናከብራለን … ምቅዋማቸው (እምነታቸው) እንዲያ ነው ማለት ነው … ለእርሳቸው … ለሰብዓዊነት የተከፈለ መስዋዕትነት ለሃይማኖት ከሚከፈል መስዋዕትነት ይበልጣል … ያም ሆኖ እውነቱ … የልጆቹ መስዋዕትነት … ለሃይማኖት የተከፈለ መስዋዕትነት መሆኑ ነው … አሸባሪው ቡድን ፤ ለዓለም ሕዝብ ከማስፈራሪያ ቃላት ጋር ባስተላለፈው የምስል ወድምፅ መልዕክቱ … በግልፅ የጠላታችን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አባላት በማለት ተናግራል … ግዳዮቹን … የእስልምና እምነትን ስለማመናቸውና ስላለማመናቸው የቁርዓን ጥያቄ እየጠየቀ የሚገድልን ቡድን እያዩ … ሌላ የሌለን ነገር ለመፍጠር … የሌለን ስም ለመስጠት መሞከር ተገቢ አይመስለንም … ከሰማዕታቱ የእምነት ጽናት ፤ ከመታመናቸው ልክ መማር ባይቻል ፤ አድንቆትን መቸር ፤ እርሱም ባይቻል እውነትን እንደወረደ መቀበል ግን ለማንም አይከብድምና ፤ … ደግሞም የክርስቲያን እምነት ተከታዮች ለእምነት ታምኖ መስዋዕት መሆን በሌላ እምነት ተከታዮች የሚያመጣው አንዳች ችግርም የለም ፤ ተከባብሮ የመኖር የቆየ በጎ ልማድንም የሚጋፋበት ሁኔታ የለም … 


እርግጥ በዚህ ዘመን (በዘመነ ሉላዊነት) የእምነት ዋጋዋ እያነሰ ሁሉም ነገር በሰብዓዊነት መጋረጃ ውስጥ እየተጠቀለለ መምጣቱ እየታየ ያለ እና የማይካድ ሀቅ ነው ፤ ዘመኑም ፍጻሜ ዘመን ነውና ይህ ሊሆን ግድ ነው … እናም ክርስቲያን ለሆነ ሁሉ … ይልቁንም ለእኛ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች የሚደንቅ አይሆንም ፤ … ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስከ አለም አቢያተ ክርስቲያናት ህብረት ያሉ ታላላቅ ተቋማት በሰው ልጆች መካከል ያሉ ማናቸውንም ልዩነቶች ለማጥፋትና አንድ ዓለምን ለመመስረት ፤ ግልጥና ስውር እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ ፤ ያም ቢሆን ፤ አስተዋይና አመዛዛኝ አእምሮ እንዲሁም ያሻውን የሚመርጥበት ነጻ ፈቃድ ከፈጣሪው የተቸረ የሰው ልጅ እንደሚመርጠው የሕይወት ጎዳና መለያየት ፤ የሕይወት አቅጣጫውም እንደሚለያይ አይጠረጠርም፡፡ የልዩነታችን እውነታ እንዳለ ሆኖ ታዲያ ፤ በተለይ በሀገራችን በኢትዮጵያ አሁን አሁን ፤ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ከሌሎች የእምነት ተከታይ ወገኖቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ፤ አንድነታችንን ፤ መተሳሰባችንን ፤ መከባበርና መገናዘባችንን የምናሳይበት መንገድ ሊጤን የሚገባው ነው ፤ … “እግዚአብሔር በስጋ መገለጡን (መውረድ መወለዱን) የማያምን ከእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም” እንዲል መጽሐፍ …


ወንጌልና የአባቶቻችን ትውፊት የሚያስተምረን ፤ አንድ ክርስቲያን ከምንም ነገር አስቀድሞ ክርስቲያን መሆኑን ነው ፤ የአገር ተወላጅነት (ኢትዮጵያዊነት) ወይም ማንኛውም ሌላ ዓይነት እሴት ዋጋ ሊኖረው የሚችለው ከክርስትናችን ጋር ከሚፈጥረው ዝምድና አንጻር ብቻና ብቻ ነው ፤ … እንዲያ ባይሆን ኖሮ ፤ ሀገራችን በሰማይ እንደሆነ ያስተማሩ ፤ እነ ቅዱስ ጳውሎስ ክርስትናቸውን ከይሁዲነታቸው አስበልጠው ሁሉን ትተው ባልተሰደዱ ነበር  ፤ ተስአቱ ቅዱሳንም ሮም መከራ ባጸናችባቸው ጊዜ ሀገራቸውን ጥለው በባሕልም በቋንቋም ወደማትመስላቸው ወደ ኢትዮጵያ ባልፈለሱም ነበር ፤ … በአጭሩ ፤ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ እንጂ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ሊኖር አይችልም ፤ አስቀድሞ ክርስቲያን ከዚያ ደግሞ በትውልድ ስፍራው ኢትዮጵያዊ … በአጠቃላይ … ክርስትና ላይ ያልተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት ክርስትናን ወደ መካድ ማድረሱ አይቀሬ መሆኑ ሊስተዋል ይገባል፡፡ በአጭሩ በሃይማኖት ዋጋ ፤ ባሕልን ዘርንና አብሮ መኖርን ለመግዛት ፤ ለማጠንከርና የማንነት መሰረቶች ለማድረግ መንቀሳቀስ ፤ መጨረሻው የክርስትናን ፋይዳ ከህልውና አስኳልነት ወደ ኮስሜቲክ ማጊያጌጫነት ወደ ማኮሰስ ያደርሳል፡፡

ለምሳሌ … የቀድሞው የሀሰት መረጃ አያስፈልግም ከሚሉት ወገን የሆነ … “ፍቅራችንን በውሸት ሃውልት ላይ አናቆምም!!” … በሚል ርዕስ … በአካል ንጉሴ በተባሉ ሰው የተጻፈን አጭር ጽሑፍ ፤ የተወሰነ ክፍል እናሳያችሁ … ጽሑፉ ስለመቻቻል እያብራራ ነው … “የኛ ግን ከዚህ ይለያል” (የእኛን መቻቻል ማለታቸው ነው) “ሰዎች እዚህ እኮ /ወሎ ማለቴ ነው/ “አይ ይህ ሃይማኖት አልከፈለኝም (አላዋጣኝም ማለታቸው ነው)  ቀይሬ ልሞክረውብሎ የሌላኛው ሰው ቤተ እምነት ውስጥ የምታገኙት ሚስቴ እምነቷ ሌላ ነው የኔ ደግሞ ወዲህ ነው፡፡የሚል ጋሽ ስብሃት እንዳለውእግዚአብሔር ይመስገን መስጊድ ተሰራልን አልሃምዱሊላሂቦታችን በሰላም ገባየሚል ሉላዊነት ቀድሞ የገባው የዋህ የፍቅር ሰው ነው የማህበረሰቡን አስተሳሰብ ያነጸው … እኔ ግን አምናለሁ ፤ በኛ ዘንድ መቻቻል ሳይሆን ህይወት አለ - በቃ ኑሮ ነዋ እኛ ያለው፡፡ ለታቦት ስለት የሚያገባ ሙስሊም የሸሆችን በር የሚያንኳኳ ክርስቲያን መቻቻል ምናምን ብሎ ቃል ወይም የውሸት የፍቅር ሃውልት አያስፈልገውም” በማለት ይቀጥላሉ … እዚህ ላይ ታዲያ የጽሑፉን ሃሳብ ባናምንበትም የጸሐፊውን እምነት እንደምናከብር እንግለፅና ወደ ጉዳያችን እንመለስ … ትልቁ ነጥብ እዚህ ላይ ነው … ጸሐፊው መሬት ላይ (በሕዝቡ) መካከል ያለውን ነገር ከመቻቻል በላይ የጠነከረና እንዲያውም ሕይወት እንደሆነ ይሞግታሉ … እንደኛ አረዳድ (አመለካከት) ግን ፤ ይህ መቻቻል (መገናዘብ) አይደለም … ይህ ክርስቲያን ለሆነ ሁሉ ጥፋት እንጅ ሕይወት አይሆንም … ባጭሩ ስም ሊወጣለት ካስፈለገ … ስሙ መቀላቀል ነው … አልያም መበራረዝ … እንደሚገባንም መቀላቀል(መበራረዝ) ለማናችንም አይጠቅምም …

ስለሆነም እኛ ክርስቲያኖች ይህን መሰሉን አመለካከት ልናስተካክል ይገባል እንላለን … 60 እና 80 ዘመን በምንቆይበት ምድራዊ ሕይወታችን ስለሚሆነው አብሮ የመኖር ነገር ከመጠን ባለፈ በመጨነቅ ፤ ተስፋ የምናደርገውን ዘላለማዊ ሕይወት እንዳናጣ ፤ ሁሉን ነገር በልክ መያዝ ያስፈልጋል ፤ አብሮ መኖርን ፤ መከባበርን ፤ መተሳሰብን ፤ መገናዘብን ስናስብ ፤ …. በእግዚአብሔር በአምላካችን ፊት እንዴት እየተመላለስን እንደሆነ … ትዕዛዛቱ (ህግጋቱ) ለመንገዳችን መብራት ሆኖ እየመራን ስለመሆኑ … የቤቱ (የቤተክርስቲያን) ስርዓት ምን እንደሚል … ከሌሎች የእምነት ተከታይ ቤተሰቦቻችን ፤ ጎረቤቶቻችን ፤ የስራ ባልደረቦቻችን ፤ … ጋር ያለን ግንኙነት ፈጣሪ በሚወደው መልኩ ስለመሆኑ በተዳኝ በጥልቀት ማሰብ ይኖርብናል፡፡

በመጨረሻ … እንዲህ ማለታችንን  የጠብ አጫሪነት አድርጎ የሚወስድ አንባቢ አይጠፋምና ማሳሰቢያ ቢጤ ብናክል አይከፋምና እነሆ ፤ … የተከበራችሁ አንባብያን ሆይ … ሃሳባችን ባጭሩ … ቅድሚያ ለሚገባው ቅድሚያ መስጠትን ከሰማዕታቱ እንማር ነው! … መጻተኞች በሆንባት በዚህች ምድር ከሚሆነው ነገር በላይ ለእኛ ለክርስቲያኖች ሊያሳስበን የሚገባ የዘላለማዊ መንግስት ጉዳይ አለብን ነው! ፤ እንጅስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንድንኖር የአምላካችን ፈቃድ ይህች ናት … በሌሎች የእምነት ተከታዮች ላይ የማይገባ ጥላቻን ስለማብቀል አይደለም ፤ በተቋሞቻቸውም ላይ ግፍን ስለመፈጸምም አይደለም … ክርስትና እንዲህ ያለውን ድርጊት አያስተምርምና … እንዲያውም የክርስቲያኖችን ሕይወት የቀጠፉት ሰዎች እንኳ ድርጊታቸው የሚወገዝ ቢሆንም ቅሉ እንዲያ ያደረጉት በክፉ መንፈስ እየተመሩ በመሆኑ ፤ ልቦና እንዲሰጣቸው ምህረትንም እንዲያገኙ ከእግዚአብሔር መለመንን የሚያስተምር ነው … ክርስትና!

በቀረውስ … እውነቱን እውነት ሀሰቱንም ሀሰት ማለት ይገባል!!

ቸር ያቆዬን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡



ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ትያትር እና ትወና ምን ይላል?



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ትያትር እና ትወና ምን ይላል?
St.Jhon Chrysostom on Theatre & Art


(A translation of part of a passage)


እንግዲህ (አብዝታችሁ) ብታነቡ የጌታችን ተከታይ ሆናችኋል እርሱም ያነባ (ያለቅስ) ነበርና ፤ በአልአዛር (መቃብር ላይ) ፤ በከተማይቱ (ኢየሩሳሌም) ላይ ፤ ይሁዳም ባገኘው ጊዜ አብዝቶ አዝኖ ነበር፡፡ ብዙዎች ሲያዝን አይተውታል ነገር ግን ሲስቅም ሆነ ፈገግ ሲል ለቅጽበት ስንኳ በየትኛውም ጊዜ ያየው ማንም የለም፤ ከወንጌላውያኑ የትኛቸውም ይህን እንዳደረገ አልገለጹም፡፡ (ቅዱስ) ጳውሎስም እንዲሁ ፤ እንዳለቀሰ ፤ ለሶስት አመታት ቀን ከሌሊት (ያለመቋረጥ) እንዳነባ ራሱ ገልጿል ፤ ሌሎችም ስለርሱ ይህን መስክረዋል ፤ እንደሳቀ ግን እርሱም የትም ቦታ ላይ አልጠቀሰም ከሌሎች ቅዱሳንም መካከል ይህን እንዳደረገ የተገለጸ ማንም የለም እርግጥ ሳራ (የአብርሀም ሚስት) (እንደሳቀች) ተጠቅሷል ይኸውም በተገሰጸችበት ወቅት ነበር በዘፍ 18፡-12-16 “እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው ሳራን ለብቻዋ በልብዋ ምን አሳቃት …..” ተብሎ እንደተጻፈ ፤ እንዲሁም የኖኸ ልጅ በተመሳሳይ ስለመሳቁ ተጽፏል ፤ ይህን ባደረገበት ወቅት ግን (በአባቱ ተረግሟልና) መጨረሻው ነጻነቱን በባርነት መለወጥ ሆነ፡፡


እንዲህ የምላችሁ ሳቅ (ጨዋታ) የተባለን ሁሉ ለመኮነን አይደለም ፤ አእምሯችሁ በከንቱነት ፤ በዋዛ ፈዛዛ እንዳይጠመድ ለማቀብ ነው እንጂ እስኪ ልጠይቃችሁ በምቾት የምትንደላቀቁና በከንቱነት የተዘፈቃችሁ ሆናችሁ ሳለ በሚያስፈራው (የጌታችን) የፍርድ መንበር ፊት ቆማችሁ እዚህ (በምድር) ላይ ሳላችሁ ስለሰራችሁት ነገር አንድ በአንድ አትጠየቁምን? በእርግጥ እንጂ … ምክንያቱም አውቀን በድፍረት ስለሰራነውም ሆነ ከአቅማችን በላይ ሆኖብን ስለበደልነው በደል ምላሽ እንድንሰጥ እንጠየቃለንና (አውቀን የሰራነው ብቻ ሳይሆን ሳናውቅ የበደልነውም ጭምር ያስጠይቀናልና … “በራሴ አንዳች አላውቅም ነገር ግን ይህ ምክንያት ሆኖኝ ከፍርድ አላመልጥም” እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ ) ወዲህም ጌታ በወንጌል  በሰዎች ፊት የሚክደኝን ሁሉ እኔ ደግሞ (በሰማዩ) አባቴ ፊት እክደዋለሁ እንዳለ ማቴ 10፡-32 ፤ አለጥርጥር ማናችንም ጌታን ወደን አንክደውምና አውቀንና ፈቅደን አናደርገውም ፤ ነገር ግን ይህም ቢሆን ከቅጣት አያድነንምና ይህንንም አስመልክቶ መልስ መስጠት ይኖርብናል፡፡

 
የምትጠየቁበት ነገር እንዲህ እጅግ የበዛ ሆኖ ሳለ ታዲያ እየሳቃችሁና ከንቱ ብልጣብልጥነት እየተናገራችሁ እንዲሁም ለድሎት ራሳችሁን እየሰጣችሁ ትቀመጣላችሁን? ይህን ማድረግ ትቼ ባዝንና ብተክዝ ምን ዋጋ አለው? የሚል ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እጅግ ክፍተኛ ዋጋ አለው እንጂ! እንዲያውም ያለው ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ዋጋውን በቃላት መግለጽ ያዳግታል፡፡ ምክንያቱም በምድራዊ ችሎት ፊት ልቅሷችሁ ምን ቢበዛ ከተፈረደባችሁ በኋላ ከቅጣታችሁ ልታመልጡ አትችሉም ፤ ነገር ግን (በሰማያዊው ችሎት) በተቃራኒው ጥቂት ብትቆረቆሩ (ብታዝኑ) ፍርዳችሁ ተፍቆ ይቅርታን ታገኛላችሁ፡፡ (“ዛሬ የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው መጽናናትን ያገኛሉና” ማቴ 5፡-4) እንደተባለ … ስለሆነም የሰውን ሁሉ መዳን የሚወድ ክርስቶስ እንድናዝን (እንድንጸጸት) አብዝቶ ይሞግተናል ፤ ይህ ( ለም) የሳቅ (ኮሜዲ) ፤ የቲያትር አምባ አይደለምና በሚስቁት (በሚያላግጡት) ላይ ይፈድባቸዋል፡፡ የመጣነውም ለከት አልባ በሆነ ሁኔታ ልንስቅና ልንዝናና አይደለም ዘወትር እዳ በደላችንን  በማሰብ  በሐዘን በመኖርና ምህረትንም በመሻት ፤ እሮሮ በማብዛት ሰማያዊውን መንግስት እንድንወርስ ነው እንጅ ፡፡ በንጉስ ፊት በምትቆምበት ጊዜ ጥቂት ፈገግታ ለቅጽበት ስንኳ በፊትህ ላይ እንዲታይ አትፈቅድም ፤ ግን (ይህ ከሆነ ዘንዳ) ታድያ የመላእክት ጌታ በአንተ ዘንድ አድሮብህ ሳለ በመራድና መንቀጥቀጥ እንዲሁም ራስህን በመግራት አደግድገህ ከመቆም ይልቅ በአንተ እንዳዘነብህ እያወቅህ ትስቃለህን? በበደልህ ካሳዘንከው ይልቅ ይህን በማድረግህ ይበልጥ እንደምታስቆጣው አታስተውልምን? እግዚአብሔር ከበደለኞች ፊቱን አይመልስምና፤ ነገር ግን በሐጢአታቸው የማይደነግጡትን (ይተዋቸዋል) ፡፡


በከንቱ ሀሳብ ከመጠመዳቸው የተነሳ ይህን ሁሉ ከተባሉ ፤ (ካወቁ) በኋላ እንኳ እግዚአብሔር ከለቅሶስ በየትኛውም ጊዜ  ይሰውረኝ በዘመኔ እንድስቅና እንድጫወት ያድለኝ እንጂ የሚሉ አንዳንዶች አሉ፡፡ እንዲህ ካለው አእምሮ ይልቅ የጨቅላ አስተሳሰብ ሊባል የሚችል ሌላ ምን አለ? ምክንያቱም በከንቱ ጨዋታና ዋዛ ፈዛዛ እንድንጠመድ  የሚያበረታታን እግዚአብሔር አይደለም ፤ ጥንቱን የሰውን ልጅ ከጽድቅ ስራ ሁሉ የሚያዘገይ ሰይጣን እንጅ … ሲጫወቱ የነበሩት እነማን እንደሆኑ (መጨረሻቸውም ምን እንደሆነ) እነሆ አድምጡ ፤ እንዲህ ተብሏልና ሕዝቡ ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፣ ሊጫወቱም ተነሱ በሰዶም የነበሩት እንዲህ ነበሩ ፤ በጥፋት ውሃ ዘመን የነበሩት (ሰዎች) እንዲህ ነበሩ፡፡ በመታበይ ፣ በጥጋብና በዳቦ ምላትም ሆነው በዝሙት ፍትወት ተቃጠሉ፡፡ በኖህ ዘመን የነበሩት (ኖህ) መርከቡን ሲያበጅ ለብዙ ዘመናት እየተመለከቱት (እንኳ) ሊመጣ ያለውን (ጥፋት) ሳያስተውሉ በከንቱ ፌሽታ (ጭፈራ) ሆነው ኖሩ፡፡ ስለዚህም ምክንያት ደግሞ ማየ ዓይህ መጥቶ ጠራርጎ ወሰዳቸው፤ በቅጽበትም አለምን ሊያጠፋት በቃ፡፡


ስለዚህም ከዲያቢሎስ የምታገኟቸውን ነገሮች ከእግዚአብሔር አትጠይቁ፡፡ እግዚአብሔር የሚሰጠው የተጸጸተና የተሰበረ ፣ የነቃና የደነገጠ ንስሐንና ወቀሳንም የተመላ ልብ ነው፡፡ እኒህ የእርሱ ስጦታዎች ናቸው ፤ ደግሞም ለእኛ እጅጉን የሚያስፈልጉን እነርሱ ናቸው፡፡ አዎን! ብርቱ ጦርነት በእኛ ዘንድ ነው፤ ፍልሚያችን ከረቂቃን ኃይላት ጋር ፤ ግድድራችን ከአመጸኞች መናፍስት ጋር   ውጊያችን ደግሞ  ከሥልጣናትና ከጨለማ ገዥዎች ጋር ነው፡፡ ኤፌ 6፡-12 ፤ በማስተዋል ፤ በሙሉ ንቃትና በዝግጁነት ሆነን ብንገኝ ይህን አውሬያዊ ሌጊዮን ለመቋቋም ያስችለናልና ለኛ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በማሽካካትና በቧልት ብንጸመድ ሁሌም ነገሮችን ንቀንና አቃለን እያየን (ብንቀመጥ) ፍልሚያው ገና ሳይጀመር በገዛ ስንፍናችን ፈጽመን እንሸነፋለን፡፡


አለማቋረጥ በመሳቅ ስጋችንን በማስደሰትና በድሎት መኖር ለኛ አይገባም ፤ ይህ ግብር ለዚህ ድርጊት ራሳቸውን የጸረቡ የአመንዝራ ሴቶች ፤ በየመድረኩ የሚታዩ ሸንጋዮችና ደም መጣጮች ግብር እንጅ ፤ ለገነት የተጠሩት (ግብር) አይደለም ፤ በሰማያት ወዳለችው ከተማ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው አይደለም በዲያቢሎስ ወገን ራሳቸውን ያሰለፉት ነው እንጅ ፤ መንፈሳዊ እቃ ጦር የታጠቁት አይደለም፡፡ ዲያቢሎስ የክርስቶስን ወታደሮች ያዳክም ዘንድ ፤ የቀደመ ጥብአታቸውንም ይፈታ ዘንድ ይህን በየመድረኩ የሚሠራ ከንቱነት ፤ ሽንገላና ማስመሰል ጥበብ (አርት) እንዲሆን (እንዲባል) አደረገው፡፡ ለዚህ ዓላማው ሲል በከተሞች የቲያትር ቤቶችን ሰራ እነዚህን አለሌዎችም (ዘፋኞችንና ተውኔተኞችን) አሰልጥኖ ሲያበቃ እነርሱ በሚያደርሱት እኩይ ተጽእኖ መላው ከተማ እንደዚያ ለ (የርኩሰት) ወረርሺኝ እንዲዋጥ ብሎም ፤ ቅ/ጳውሎስ እንድንሸሻቸው ያዘዘንን እነዚያኑ ነገሮች - ‹‹ከንቱ ንግግርና ቧልት ››- እንድንከተል (በዚህ መንገድ) ይገፋፋናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ይበልጥ አሳሳቢ የሆነው የሚሳቅበት ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚያ ባእድ የሆኑትን ድርጊቶች የሚተውኑት ተውኔተኞች የጽርፈትና የርኩሰት ንግግር ከአንደበታቸው በሚወጣበት ወቅት ከንቱነት ከተጠናወታቸው መካከል በርካቶች ይስቃሉ ደስም ይሰኙባቸዋል ፤ ሊወግሯቸው ሲገባም ያጨበጭቡላቸዋል ፤ በመሳቃቸው ምክንያትም የጥፋት እሳትን በራሳቸው ላይ ያመጣሉ፡፡ ምክንያቱም ለእነዚህ ሰዎች ሙገሳን በመቸራቸው ሰዎቹ ክፋትን እንዲናገሩ ምክንያት ሆነዋልና ….. ስለሆነም ለዚህ የተዘጋጀው ቅጣትና ፍርድ (ከተናጋሪዎቹ ይልቅ በአጨብጫቢዎቹ ላይ ይበልጡኑ) ሊበየንባቸው ይገባል፡፡ እኒህን (ርኩሰቶች) የሚያይ ተመልካች ባይኖር ኖሮ (ተውኔቱን) የሚተውንም ባልኖረ ነበርና ፤ ነገር ግን ስራችሁን ፣ መደብራችሁን ፣ ገንዘባችሁን ፣ ባጭሩ ያላችሁን ሁሉ ሰውታችሁ (እዚያ ለመገኘት) ስትቻኮሉ ሲመለከቱ ፤ ይህን ድርጊት ለመፈጸም ከፍ ያለ ተነሳሽነት ይኖራቸዋል ፤ በብርቱ ትጋትም (ተውኔቱን) ለማከናወን ይባትላሉ፡፡


ይህንን ያልኩት (ተዋንያኑን) ከወቀሳ ነጻ ላወጣቸው አይደለም፤ ለዚህ ስርአት አልበኝነት በዋነኝነት ምክንያትና ስር እየሆናችሁ ያላችሁት እናንተ እንደሆናችሁ ትረዱ ዘንድ ነው እንጂ ፤ እለቱን ሙሉ በነዚህ ነገሮች ተጠምዳችሁ ጊዜያችሁን የምታጠፉ እናንተ፣ በትዳር ውስጥ በክብር የተጠበቁትን ነገሮች በማራከስ የምታራ ፤ ታላቁን የተክሊል ምስጢር በአደባባይ ማላገጫ እንዲሆን የምታደርጉ (እናንተ ናችሁና)፡፡ እኒህን (ጸያፍ) ድርጊቶች የሚተውነው የናንተን ያህል ጥፋተኛ አይሆንም ፤ በነዚህ ነገሮች እንዲቀልድ የምትገፋፉት እናንተ ናችሁና ፤ እንዲያውም መገፋፋት ብቻ አይደለም ደግሞም በሁኔታው በመደሰትና በመሳቅ የቀረበውንም ድርጊት በማሞካሸት፣ እነዚህ የዲያቢሎስ መደብሮች እንዲጠናከሩ በከፍተኛ ተነሳሽነት ትንቀሳቀሳላችሁ፡፡


እንግዲያው እስኪ ንገሩኝ? ሴት ልጅ (ሚስት) በዚያ (በቤተ-ተውኔት) ስትሰደብ (ስትነወር) ስታዩ (ቆይታችሁ) በምን አይናችሁ እቤት ያለች ስታችሁን ታይዋታላችሁ? ተፈጥሮዋስ እንዲህ በአደባባይ ሲነወር (ስትመለከቱ) እቤት ያለችውን (የህይወታችሁን) አጋር አስባችሁ እንዴት ልታፍሩ (ልትሸማቀቁ) አልቻላችሁም? የተፈጸመው ትወና (acting) እኮ ነው ደግሞ እንድትሉኝ አልወድም! ይኸው ‹ትወና› ብዙዎችን ዘማውያን አድርጓልና ፤ የብዙ ቤተሰቦችን ኑሮ አፍርሷልና፡፡ እንዲህ እጅግ የከፋ የዝሙት ድርጊት (ትወና) ሲቀርብ (ርኩሰትነቱ ታውቆ) እንደ ጢአት ከመቆጠር ይልቅ በፉጨትና በጭብጨባ እንዲሁም በከፍተኛ ሳቅ የሚታጀብ በመሆኑ … ከሁሉም በላይ ደግሞ በዚህ አብዝቼ አዝናለሁ፡፡ ምንን ትላላችሁ?! የሚደረገው ትወና ነውን? ሁሉም ህግጋት ሰዎች እንዲሸሹዋቸው የሚያዟቸውን እነዚህን ድርጊቶች አስመስለው ለመተወን ሲሉ በብርቱ ደክመዋልና ስለዚሁ ምክንያት (እኒህ ሰዎች) አስር ሺህ ሞት ይገባቸዋል፡፡ ድጊቱ መጥፎ ከሆነ ይህንኑ ማስመሰልም ደግሞ መጥፎ ነውና፡፡ እኒህን የዝሙት ትዕይንቶች የሚተውኑ ግለሰቦች ምን ያህል ዘማውያንን በተውኔታቸው እንደሚያፈሩ ፤ ታዳሚዎቻቸውን እንዴት በድርጊታቸው ደፋርና ፈሪሀ-እግዚአብሔርን የማያውቁ እንዲሆኑ እንደሚያደርጓቸው … ገና ወደዚህ (ጉዳይ) አልደረስኩም ፤ እንዲህ አይነት (አስነዋሪ) ድርጊቶችን ተቋቁማ ከምትመለከት አይን የባሰ አመንዝራነትንና ድፍረትን የተሞላ ነገር የለምና፡፡


አንተ ሴት ልጅ በገበያ … ኧረ እንዲያው በቤት ውስጥ እንኳ ልብሷን ተገፋ እርቃኗን እንድታያት አትወድም ፤ ከባድ ድፍረት ነው ብለህ ትቆጣለህ እንጂ፡፡ ነገር ግን (መልሰህ) የወንዶችና የሴቶች ተፈጥሮ ላይ ልታላግጥ ፤ አይንህንም ልታረክስ ወደቲያትር ትሄዳለህን? ‹ልብሷን የተገፈፈችው (እኮ) አመንዝራ ነች› በማለት (ምክንያት ልትደረድር) አይገባም ፤ የአመንዝራይቷም ሆነ የነጻይቱ ሴት የተፈጥሯቸው ባሕርይ አንድ ነው፤ አካላቸውም አንድ ነው፡፡ ይህ ስህተት ካልሆነ ታዲያ ይኸው ድርጊት በገበያ ሲፈጸም ብትመለከት ራስህን ከዚያ ለማራቅና ነውሩን የፈጸመችውንም ሴት ልታርማት የምትፋጠንበት ምክንያቱ ምንድን ነው? ወይስ ብቻችንን ስንሆን ድርጊቱ ነውር የሚሆን ፤ አንድ ላይ ተሰባስበን ስንቀመጥ ደግሞ በዚያው ልክ የማያስነውር ይሆናልን? ፈጽሞ! ይህ በርግጥም ነውርና ውርደት እንዲሁም ፍጹም እብደት ነው ፤ እንዲህ አይነት በደል ሲፈጸም ታዳሚ ከመሆን ይልቅ አይንን በጭቃ መቀባት ይሻላል፡፡ ሴት ልጅ እርቃኗን ሆና ከማየትና ዝሙት የተመላ ትእይንት ከመመልከት የበለጠ ጭቃው አይንን ፍጽሞ ሊጎዳ አይችልም፡፡ ለምሳሌ ሲጀመር እርቃን መሆን የመጣበት ምክንያት ምን እንደሆነ አድምጥ ፤ ይህ ውርደት የተከሰተበትን መንስኤ አንብበህ (ተረዳ)፡፡ በውኑ እርቃን መሆን እንዴት ሊከሰት ቻለ? የኛ መተላለፍ (መሳት) ና የዲያቢሎስ ምክር (ውጤት) ነው፡፡ እናም ከመነሻው ስንኳ አንስቶ ይህ የርሱ (የዲያቢሎስ) ሸር ውጤት ነው፡፡ ቢያንስ ግን (አዳምና ሔዋን) እርቃናቸውን በሆኑ ወቅት አፍረው ነበር ፤ አንተ ግን በዚያ ትኮራለህ፤ ሐዋርያው እንዳለው ‹ክብርህ በርኩሰትህ ሆኗል›፡፡


በዚህ የክፋት ስራ ቆይተህ (ቤትህ) ስትመለስ ታዲያ ሚስትህ ከዚያ አንስቶ እንዴት ታይሃለች?  በአደባባይ የሴትነትን ተፈጥሮ እንዲ አዋርደህ በአየኸውም ነገር የአመንዝራዎች ምርኮኛና ባርያ ሆነህ ስታበቃ በምን ሁኔታ ትቀበልሃለች? እንዴትስ ታናግርሃለች?


እኒህን ነገሮች በሰማህ ጊዜ ያዘንክ ከሆነ ላመሰግንህ እወዳለሁ ፤ ‹‹ደስ የሚያሰኘኝ ማን ነው? በእኔ ምክንያት ያዘነ ነው እንጂ›› (ይላልና)፡፡ ስለሆነም በድርጊቶችህ ማፈርና መጸጸትን አታቁም፤ እንዲህ ካሉ ነገሮች የሚመጣው ጥልቅ ሐዘን ላንተ ወደ መልካም ለመለወጥ መነሻ ይሆንሀልና፡፡ ለዚህ ምክንያት ስል ፤ ጠለቅ አድርጌ በመብጣት እነርሱ ካሰከሩህ (የርኩሰት) መርዝ ነጻ አወጣህ ዘንድ እንዲቻለኝ የተግሳጼን ቃላት ጠንካራ አድርጌያቸዋለሁ ፤ ወደ ንጹሁ የነፍስ ጤንነት እመልስህ ይቻለኝ ዘንድ ፤ እግዚአብሔር እንደፈቀደ ሁላችንም በተቻለን መጠን ከእርሱ በመቋደስ ለመልካም ምግባራት የተዘጋጁትን ሽልማቶች መቀዳጀት እንችል ዘንድ ጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ፍቅር ከሁላችን ጋር ይሁን ፤ አሜን፡፡


ወስብሐት እግዚአብሔር!



ምንጭ፡- ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜ ዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ፤ ማቴዎስ 2፡-1-2 ፤ ገጽ 64-67 ፤ Christian Classics Ethereal Library New York: Christian Literature Publishing Co., 1886