Pages

Friday, July 12, 2013

ዘመን ተሻጋሪው የሁለት ከተሞች ጠብ …

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

ዘመን ተሻጋሪው የሁለት ከተሞች ጠብ …
ግለኝነትና ኢኮኖሚያዊ ስኬት በነገሱበት ዘመን ድህነት እና ኋላቀርነት ሲታወሱ
‘‘ሁለት ዓይነት ፍቅሮች ሁለት ዓይነት ከተሞችን መሠረቱ ፤
ፈጣሪን እስካለመታዘዝ ፤ እስከመናቅና እስከመካድ  የደረሰ ራስን መውደድ የመሠረተው ምድራዊ ከተማ
አና ራስን እስከመካድ የደረሰ ፈጣሪን መውደድ የመሠረተው ሰማያዊ ከተማ’’
ቅዱስ አውግስቲን


ለዘመናዊ ስልጣኔ ፤ ቴክኖሎጅ ለደረሰበትም ከፍታ እንግዳ የሆነና እንደ እኛ ሀገር ባለ … ስልጣኔ ባልደረሰው ፤ ኋላቀር የአለም ጥግ … የተወለደን ሰው ፤ በሰላም ከሚኖርባት ደሳሳ ጎጆው ፤ ድንገት አንስተው … ማንሃተንን በመሰለ ትልቅ ከተማ ውስጥ ቢጨምሩት … የምዕራቡ ዓለም ከደረሰበት ዕድገት … አይን ገብ ከሆነው ከባቢው የተነሳ … ፍርሃትና አድናቆት … ድንጋጤም ውስጥ መግባቱ …  ‘በህንጣ ላይ ህንጣ… በህንጣ ላይ ህንጣ… እንደው ምድረ ገነት አይደለም እንዴ?’ በማለት መደመሙ አይጠረጠርም። … ነገር ግን ከዚህ የመደነቅና የመደመም ስሜቱ ቀስ በቀስ ሲወጣ … ቀድሞ እንዳሰበውና እንደገመተው … ኋላቀርና ስሜት አልባ እንዳልሆነ ያረጋግጣል ፤ … እንዲያውም አብረቅራቂ በሆነው ቁሳዊ ውበት ተማርኮና ወረተኛ በሆነ ስሜት ታስሮ እስካልቀረ ድረስ … ስሜቱን ተቆጣጥሮ ፤ የነገሮችን መነሻና መድረሻ ለማየት አይኑን በእውነተኛ አመክንዮዎች ለሚያማትር  አስተዋይ … ያላግባብ በጠላትነት የፈረጅነው ድህነት እንደምናስበው ጠላታችን አለመሆኑን ይረዳል። ለአፍታ እስኪ … ከስልጣኔ መነሻ ጋራ ተያይዘው የሚነሱ እውነታዎችን ክርስቲያናዊ በሆነ አተያይ ልንመለከታቸው እንሞክር … የት እንደሚያደርሱንም እንይ …

መጽሐፈ ሔኖክ አስረግጦ እንደሚገልጠው አብዛሃኛውን የሰው ልጅ ስልጣኔ (የጦር መሳሪያ አሰራርን ፤ ኮከብ ቆጠራን ፤ አስማትን ፤ ጌጣጌጥ መስራትን ፤ ያንዱን ጽንስ በሌላው ማህጸን ማሳደርን ፤ ስር መማስና ቅጠል መበጠስን ፤ … ) ለሰው ልጅ  ያስተማሩ … ፍጹም ስለሆነ መተላለፋቸው ምክንያት ወደ ጥልቁ የወረዱ … በዚያም ለሺህ ዓመት እስር የተፈረደባቸው … ርኩሳን መላዕክት ናቸው። ሔኖክ“… አዛዝኤል ሰይፍንና ሾተል መስራትን ጋሻ መሰጎድን ጥሩር መልበስን አስተማራቸው … አምባር መስራትን ጌጥ ማጌጥን ዓይን መኳልን … ቅንድብ መሸለልን … የተመረጠ የከበረ ከሚሆን ከደንጋይ የሚበልጥ ደንጊያን … ከብረት የሚበልጥ ብረትን … ከብረት የሚበልጥ ብርን … ከብር የሚበልጥ ወርቅን … ከወርቅ የሚበልጥ ዕንቁን አሳዩዋቸው … እግዚአብሔር ነጭ ጥፍር ቢፈጥር በእንሶስላ ማቅላትን በደንጓ መጠቆርን በሕናም … የአለምን ለውጥ አሳዩዋቸው … ያንዱን ጽንስ ባንዱ ያንዱን ጽንስ ባንዱ ማኅፀን ማሳደርን … ፅኑዕ በደል ብዙ ሰሰንም ተደረገ ሳቱ አመነዘሩም ሥራቸውም ሁሉ ጠፋ … አሚዛራክ ጋኔን የሚስቡን ምትሐት ማሳየትን አስተማረ … ሥር የሚምሱትን ቅጠል የሚበጥሱትን አስተማረ … አርሚሮስ ምታት ማሳየትን አስተማረ … በራቅኤልም ኮከብ የሚያዩትን እንዲህ ያለ ሲወጣ እንዲህ ያለ ይደረጋል ማለትን … አስራድኤልም ጨረቃ በዚህ ስትወጣ ምህረት በዚህ ስትወጣ መዓት ይሆናል እያለ አስተማረ … በሰዎች ጥፋት ሰዎች ጮኹ ቃላቸውም ወደ ሰማይ ደረሰ …’’  እንዳለ (ሄኖክ 2፦18-26 ትርጓሜ)

በትውፊት እንደምንረዳው ትውልደ ሴት በቅዱሳን መላዕክት አኗኗር አምሳል ንጽህ ጠብቀው በምስጋናና በጸሎት በደብር ቅዱስ  ይኖሩ ነበር እንጅ በምድራዊ ስልጣኔ የተሳቡና የተወሰዱ አልነበሩም ፤ ከሴት አስቀድሞም  የአቤል የሙያ መስክ  ከወንድሙ ከቃየን  በተቃራኒ የተቀመጠ ነበር። የቤተክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊው ዮሴፈስ ፤ አንቲኪዩቲስ በተሰኘው የመጀመሪያ መጽሐፉ ፤ በምዕራፍ ሁለት ፤ በመጀመሪያው አንቀጽ ላይ እንደሚጠቅሰው ፤ አቤል … ስሙ ድህነትና ሀዘንን የሚገልጽ ሲሆን ፤ ቃየን … ደግሞ ስሙ ትርፍና የራስ ማድረግን የሚገልጽ ነው። አቤል ከብቶችን በማርባት የሚኖር ፤ አርብቶ አደር የነበረ ሲሆን ፤ ቃየን ደግሞ መሬትን አርሶ የሚኖር ፤ አርሶ አደር ነበረ … ይህንንም ትርፋማነትን ሽቶ ያደርገው ነበር። … በክፉ ስራው ከተረገመና መሬት ኋይሏን ከከለከለችው በኋላም ተቅበዝባዥ ሆኖ በሌላው ወዝ ለመክበርና የሌላውን ለመንጠቅ/የራሱ ለማድረግ ሲደክም ኖሯል ፤  ይኸውም ኋላ ለተነሱ አራጣ አበዳሪዎችና ሳይደክሙና ሳይለፉ በሌላው ጉልበት ባለጸግነትን ለሚሹ ሰዎች መንገድ አመላካች ሆኗል … እዚህ ላይ ታዲያ እርሻ የምድራዊ የስልጣኔ መጀመሪያ መሆኑን ልብ ይሏል ፤ … ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ  … አርብቶ አደርነትነትን እንደ ሙያ ያየነው እንደሆነ ተቀማጭ የሚባል ነገር የለውም ፤ በተቃራኒው አርሶ አደርነትን ስንመለከት ተቀማጭ የሚሆን ምርትን በተጨማሪነት ይሰጣል … ይኸውም ከአርብቶ አደርነት ሙያ ጋራ ባንጻራዊነት ስንመለከተው … የሰውን ልጅ ስግብግብነትና ቁጥጥርን ለመሰሉ እንግዳ ባህርያት የሚያጋልጥ ሆኖ እናገኘዋለን። … ወዲህም ደግሞ ስግብግብነት እና ቁጥጥር የካፒታሊዝም ስርዓት መገለጫዎች ናቸው።

አቤልንም ተከትለው የተነሱ ደጋግ አባቶችን ፤ አብርሃም ፤ ይስሃቅ ፤ ያዕቆብ ፤ ኢዮብና መሰሎቻቸውን ብንመለከት ፤ የአርብቶ አደርነትን ሕይወት የሚኖሩ ነበሩ። እንዲያውም አበ ብዙሃን አብርሃም በጊዜው በስልጣኔዋ ወደር ያልነበራትን ኡርን/ባቢሎንን ትቶ በድንኳን ውስጥ በእግዚአብሔር መንገድ ይኖር እንደነበረ ማንሳቱ ትልቅ ማስረጃ ይሆነናል … እርግጥ አባታችን አብርሃም ባለጸጋ ነበረ … ያም ሆኖ ባለጸጋነቱ ተቀማጭ በሆነ ብዕሉ የሚገለጽ ሳይሆን ፤ በተባረኩለት እንስሶቹ የሚገለጽ ነው ፤ በተጨማሪም በታሪክ የተመዘገበ ቋሚ የመኖሪያ ቦታም አልነበረውም።

ባንጻሩ ቃየንን ስንመለከት ፤ በወቅቱ በበቂ ሁኔታ ይገኙ የነበሩና ፤ በተፈጥሮ የሚበቅሉ ጥራጥሬዎችና ፍራፍሬዎች ይበቁኛል ማለትን ትቶ ፤ ስግብግብነቱ ከፈጠረበት … ተጨማሪ የማግኘት ሀሳብ የተነሳ መሬትን ማረስ የጀመረ ፤ ቋሚ የሆነ መኖሪያን በማመቻቸትና ፤ የግል ንብረትን በማፍራት መንገድ የተጓዘ ነበረ ፤ … እዚህ ላይ በምድር ላይ የመጀመሪያውን ከተማ በልጁ በሔኖስ ስም የቆረቆረ እርሱ መሆኑን ልብ ይሏል። … ይህም መንገዱ  ራስን ወደ መውደድ እንዳደረሰው … ለእግዚአብሔር ባቀረበው መስዋዕቱ … ጥሩውን ለራሱ አስቀምጦ እንክርዳዱን በማቅረቡ በግልጽ ታይቷል።

እንግዲህ … የቃየን ቤተሰብ የጥፋት ጉዞ … ቃየን ትርፍንና ሀብት ማካበትን መሠረት አድርጎ ወደ አርሶ አደርነት ሙያ በመግባቱ የሚገለፅ እንደሆነ እንረዳ። … ምድራዊ ሰዎች በምድራዊ ስልጣኔ ይሳባሉ … የእግዚአብሔር ልጆች ደግሞ ገዳማዊነትን በተላበሰና ትኩረቱ ሰማያዊ በሆነ ኑሮ ይሳባሉ። … ይህ ሲባል ታዲያ አርሶ አደርነትን እንደ ሙያ ለማውገዝ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል … ምክንያቱስ … ገበሬ ሆኖ የጽድቅን ሕይወት መምራት በሚገባ ይቻላልና ፤ ነገር ግን ለማለት የተፈለገው ከአርብቶ አደርነት ጋር ሲነጻጸር በዚህ ቁሳዊ ዘመን ላይ እንደሚታየው ያልታቀደና ያልታሰበ የምቾት ኑሮ እንደሚያስከትል አስረግጦ ለማለፍ ነው።  … ወደ እንዲህ ያለ ያልተገባ የምቾት ኑሮ የተገባ እንደሆነም … በራስ ድካም ከመኖር ይልቅ በሌላ ትከሻና ወዝ መኖርን የሚያስመርጥ ይሆናል … ፍጻሜውም የኃጢአት ስራዎችን ወደ መፈጸም ያደርሳል  … ይህም እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጅ ይኖርበት ዘንድ ካቀደው/ካዘጋጀው የኑሮ ሁኔታ ጋር በእጅጉ የራቀ ነው። …

ያም ሆኖ የቃየን ልጆች ፍላጎት ምድራዊ ስልጣኔ/ምድራዊ ጥበብ ነበር/ነው። … ከእግዚአብሔር መንገድ ርቆ ለስጋ የተመቸና የተቀናጣ ምድራዊ ኑሮ … ብዙዎች በባርነትና በጭቆና ውስጥ የሚወድቁበት ፤ ጥቂቶች የሚቀማጠሉበት ምድራዊ ስልጣኔ … በርኩሳን መላዕክት ገላጭነት የተገኘ ስልጣኔ …

ታሪክ ከመዘገባቸው ጥንታዊ ስልጣኔዎች መካከል የግብፅ ፤ የሞሶፖቶሚያ ፤ የሱመሪያ ፤ የማያ ፤ እና የአዝቴክ ስልጣኔዎች ለታሪክ ተመራማሪዎችና አርኪዮሎጅስቶች እንቆቅልሽ በሆነ መልኩ ባንዴ የፈነዱ ክስተቶች እንጅ ፤ ስልጣኔያቸው ተፈጥሯዊ በሆነ መልኩ ቀስ በቀስ የመጣ ፤ ዕድገታቸውም ሂደት በሂደት የሚገለጽ አይደለም። … ከስልጣኔያቸው በፊት በጎሳና በወንዝ የተቧደኑ ሕዝቦች እዚህም እዚያም ይኖሩ ነበረ ፤ ከዚያም በድንገት አሁን ድረስ የብዙዎችን አድናቆት የሚያተርፉ ስልጣኔዎች ተከሰቱ … ፈነዱ ቢባል ይቀላል።


ታዲያ እነዚያ ስልጣኔዎች ከወዴት በቀሉ? … ቴክኖሎጅካል ርቀታቸውንስ ከወዴት አገኙ? … መልሱ በመጽሐፈ ሔኖክ ተመዝግቦ ይገኛል … የበፊቶቹም ይሁኑ የአሁኖቹ ምድራዊ ስልጣኔዎች/ጥበባት ምንጭ … የሰውን ልጅ ከፈጣሪው በጎ ጎዳና አውጥተው በጥፋት መንገድ ለመውሰድ የማይደክሙት ርኩሳን መላዕክት ናቸው። ሔኖክ “… ያን ጊዜ ሚካኤልና ገብርኤል ዑራኤልና ሱርያል በዚህ ዓለም በግፍ የፈሰሰ ብዙ የሰው ደምን … በዚህ ዓለም የሚሰራ ግፍን ሁሉ አዩ … ለጌታቸው ለንጉሱ እንዲህ አሉት … የአማልክት አምላክ የነገስታት ንጉስ አንተ ነህና … አንተ ሁሉን መርምረህ ታውቃለህና … ከአንተም ሊሰወር የሚቻለው የለምና … አዛዝኤል ያደረገውን እይ … በዚህ ዓለም ግፉን ሁሉ እንዳስተማረ … በሰማያት የሚሰሩትን በዓለም የተሰወሩትን እንደገለጠ እይ …’’ እንዳለ (ሄኖክ 2፦27 ትርጓሜ)

የአሜሪካው የፊልም ኢንዳስትሪ/ሆሊውድ የኤሊየንን አፈታሪክ የሚያጮኸው የእነዚህን ስልጣኔዎች/ክስተቶች መነሻ ለመግለጽ እንደሆነ … ይኸውም የስልጣኔዎቹ ገላጮች ከምድር ውጭ ያሉ ኤሊየን የተባሉ እንግዳ ፍጥረታት ናቸው የሚል በሬ ወለደ ዓይነት መላምት መሆኑን ልብ ይሏል።   … ሀቁ ግን እየተስተጋባ  የሚገኘው የኤሊየን አፈታሪክ ፍጹም ውሸት መሆኑ ነው። … እንዲያውም ኤሊየን የሚሏቸው ፍጥረታት ራሳቸው የተጣሉት መናፍስት ናቸው።

እስራኤል ዘስጋ በአካባቢያቸው ይኖሩ ከነበሩ ሌሎች ሕዝቦች በተለየ በነገድ/በጎሳ ተከፋፍለው እና ምድራውያን በሆኑ ሰዎች እይታ ኋላቀር የሚባል ዓይነት ኑሮ የሚኖሩ … ለራሳቸው አስተዳዳሪ ንጉስ ያልነበራቸው ሕዝቦች ነበሩ። እንዲያም ሆኖ አምላካቸው የሰጣቸውን ትዕዛዛት የሚጠብቁ የነበሩ … ዳኝነትን የሚያደርጉ … ጥፋተኛን የሚቀጡ … ከአህዛብ ተደጋጋሚ ጥቃት ሕዝቡን የሚጠብቁ ዳኞችና መሳፍንት … አምላክ ራሱ የሚያስነሳላቸው ሕዝቦች ነበሩ። ይህም አኗኗራቸው የእግዚአብሔር ፈቃዱ የነበረ ሲሆን … የሕዝቡ ማህበራዊ ሕይወት ለምድራዊ ፍላጎቶች ብዙም ግድ የሌለውና ፤ ለገዳማዊነት የቀረበ ነበረ። … ያም ሆኖ ከጊዜ በኋላ አምላካቸው ከሰራላቸው የሕይወት ጎዳና ወጥተው የአሕዛብን አኗኗር ተመኙ … በላያቸውም ላይ ንጉስ እንዲነግስ ውዳቸው ሆነ … አምላክም ይህን ሀሳባቸውን ባይወደውም እንደ ፈቃዳቸው ተዋቸው። በነብዩ በሳሙኤል “የእስራኤል ሰዎች ሁሉ በአንድነት ተሰብስበው ወደ ሳሙኤል ወደ አርማቴም መጡ፡ እንዲህም አሉት፦ ‘ … እንደ አህዛብ ሁሉ የሚፈርድልን ንጉስ አንግስልን’ … እንዲህም ባሉት ጊዜ ሳሙኤል ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። እግዚአብሔርም ሳሙኤልን አለው ‘በእነርሱ ላይ እንዳልነግስ እኔን ናቁ እንጅ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር የሕዝቡን ቃል ስማ … ነገር ግን ጽኑ ምስክርን መስክርባቸው በእነርሱም ላይ የሚነግሰውን የንጉሡን ሥርዓት ንገራቸው’ … ሳሙኤልም የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ንጉሥን ለፈለጉ ሕዝብ ነገራቸው። እንዲህም አለ፦ ‘በእናንተ ላይ የሚነግሠው የንጉሡ ሥርዓት ይህ ነው ወንዶች ልጆቻችሁን ወስዶ ሰረገላ ነጅዎችና ፈረሰኞች ያደርጋቸዋል … እርሻውንም የሚያርሱ እህሉንም የሚያጭዱ ፍሬውንም የሚለቅሙ የጦር መሣሪያውንና የሰረገሎቹንም ዕቃ የሚሰሩ ያደርጋቸዋል ሴቶች ልጆቻችሁንም ወስዶ ሽቱ ቀማሚዎችና ወጥ ቤቶች አበዛዎችም ያደርጋቸዋል … እናንተም ባሪያዎች ትሆኑታላችሁ በዚያ ቀን ለእናንተ ከመረጣችሁት ከንጉሣችሁ የተነሳ ትጮኻላችሁ በእነዚያም ወራት እግዚአብሔር አይሰማችሁም። ለራሳችሁ ንጉሥን መርጣችኋልና’” 1ሳሙ 8፦1-ፍጻሜ ተብሎ እንደተጻፈ።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋዌው ዘመን ሳለ ጠላት ዲያቢሎስ ካቀረበለት ፈተናዎች አንዱ ‘ብትሰግድልኝ ፤ እጅ ብትነሳኝም … የዓለሙን ሁሉ መንግስታት ፤ ክብራቸውንም ሁሉ እሰጥሃለሁ’ የሚል ነበር ማቴ 4፦9 … ይህም የዚህችን ምድር ገዥ ማንነትና በውስጧም ስኬታማ ሆኖ ለመገኘት ምን ዓይነት መንገድ መታለፍ እንደሚገባው የሚገልፅ ጥሩ ማሳያ ነው። … በአርበኝነት ስም የጎረቤት ሀገራትን ድንበር በመግፋት እድገታቸውን ለማረጋገጥ የሚጥሩ ስግብግብ ሀገራት እንዳሉ እርግጥ የመሆኑን ያህል … እውነተኛ ክርስቲያኖች ይህን በመሰለው ክፉ ተግባር ውስጥ መቼም መች ሱታፌ እንደማይኖራቸው እሙን ነው። … ነቢዩ ዳንኤልና የአርማትያው ዮሴፍ በመንግስት የአስተዳደር ወንበር ላይ የነበሩ ቢሆንም መልካም በሆነው አገልግሎታቸው አብነት ሆነው የሚጠቀሱ እንጅ ስልጣናቸውን ለግል ጥቅምና ትርፍ ለሌላም ይህን ለመሰለ እኩይ ተግባር መጠቀሚያ አላደረጉትም ፤ በተጨማሪም ኑሯቸው … በተለይ የነቢዩ ዳንኤል … በመንግስት የስልጣን እርከን ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚወጡ ሰዎች/ክርስቲያኖች ከፊታቸው ስለሚጋረጥባቸው ምርጫና ፤ ሊወስኑትም ስለሚገባው ውሳኔ የሚገልጥ ራሱን የቻለ ጥሩ መምህር ነው … ስለ ስጋዊ ጥቅም ብሎ ነፍስን አሳልፎ መሸጥ አልያም ራስን ከአንበሳ መንጋ ጋር በአንድ ክፍል ማግኘት ‘‘ባለጸጋ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ከሚገባ ይልቅ ፤ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብታልፍ የቀላል’’ ማር 10፦25  እንዳለ ጌታችን።

በንጉስ ቆስጦንጢኖስ ዘመን ፤ የክርስትና ሃይማኖት አብቦ የመንግስት ሃይማኖት ለመሆን በቅቶ ነበር … ይህም በሆነ ጊዜ የእድገት ማማ ላይ ደርሶ የነበረው የሮም ስልጣኔ መክሰም ሲጀምር ባንጻሩ ደግሞ የሮሟ ቤተክርስቲያን የአውሮፓን ሀገራት … መንግስታቶቻቸውንም ጭምር በስሯ ማስተዳደር ጀምራ ነበር … የሐዝቡም አኗኗር በአንጻራዊነት ቀለል ያለ … ለመሬት የቀረበም ሊባል የሚችል የነበረ ሲሆን … ባጠቃላይ ቤቴክርስቲያኗ በምዕራቡ አለም የነበራትን ቁጥጥር እስካጣችበት ጊዜ ድረስ (ክርስትና በተስፋፋበት ዘመን) … የካፒታሊዝም ስርዓት … መለያውን ቴክኖሎጅካል ቁሳቁስ ያደረገው ዘመናዊው የስልጣኔ ጽንሰ ሃሳብ … ወ.ዘ.ተ ለስም አጠራራቸው እንኳን መገኛ አልነበራቸውም።

በመካከለኛው ዘመን ይህ ቀለል ያለ የአኗኗር ዘይቤ እና ሃይማኖታዊ ቅድስና የየትኛውም ማህበረሰብ ኑሮ መገለጫ ሆኖ በታሪክ ድርሳናት ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ሀቅ ሲሆን … ዘመናዊ የታሪክ ተመራማሪዎች የማይገባውን ስም በመስጠት የጨለማው ዘመን በማለት ይጠሩታል … ሆኖም ይህ ቅፅል ለክርክር በእጅጉ ክፍት ከመሆኑም በላይ ከክርስቲያናዊ አተያይ ያየነው እንደሆነ ኋላቀርና የጨለማ ዘመን ለመባል የሚገባው ይህን የኛን ዘመን  ሆኖ እናገኘዋለን። … የሰው ልጅ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግራ በሚያጋቡና ውስብስብ በሆኑ ቁሳቁሶች እንደተከበበ ህጻን እየሆነ … አልፎ ተርፎም ቁሳቁሶቹ እንኳን እንዴት እንደተሰሩ ግድ የማይሰጠው … የሰጡትን ያለምንም ጥያቄ የሚቀበል ሆኗልና።

በተመሳሳይም በሀገራችን የሚገኙ አንዳንድ ምሁራን ንጉስ ፋሲል ኢየሱሳውያንንና የውጭ ሚሺነሪዎችን ከሀገራችን ጠራርጎ ያስወጣበትን ዘመን የኢትዮጵያ የጨለማ ዘመን በማለት ይፈርጁታል … እኛ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ግን … ንጉሱ … እንደ አባቱ በኢየሱሳውያኑ ሳይታለል … ለሃይማኖታዊ ቅድስናና ለሀገራዊ እሴቶች መጠበቅ በቁርጠኝነት በመቆሙ … ከቁሳዊ እድገትም በላይ ትልቅ ዋጋ ያለው ውሳኔ እንደወሰነ እናምናለን። … ይህም የዚህ ዘመን … የታሪክ ጽንሰ ሃሳብ … መሰረቱን ያደረገው በእምነት የለሽነትና በቁሳዊነት ላይ ለመሆኑ ሁነኛ ማረጋገጫ ይሆነናል። … እምነት የለሽነትና ቁሳዊነት ገና ያልገነኑበት ያ ዘመን ኋላቀርና የጨለማ ዘመን ሲባል … እውቀት አልባ ነገር ግን በቁሳቁስ የተጨናነቀው ይህ ዘመን ደግሞ የስልጣኔ ዘመን ይባላልና።

በንጉሱ በሰሎሞን ዘመን እስራኤላውያን በጣኦት አምልኮ መውደቃቸው … ከዚሁ ቁሳዊ ስልጣኔ ፤ ይልቁንም ብዕልን/ገንዘብን ከማከማቸታቸው የተነሳ በራሳቸው ላይ ያመጡት ዕዳ ሲሆን ፤ ይህም ከእግዚአብሔር የጽድቅ መንገድ ጋር የማይጣጣም … ምድራዊ ፍላጎት ያየለበትና … የዲያቢሎስ ተፅዕኖ የበረታበት አካሄድ ነው። …
የሰው ልጅ መታመኑን በራሱ የስራ ፍሬዎች ባደረገ መጠን ፤ ለእግዚአብሔር ፈቃድ መገዛቱ ይቀንሳል … ተፈጥሮን የሚቆጣጠርበትንም መንገዶች ባቀደ መጠን ፤ ያልተገመተ ክስተት የሚባል ነገር ያጣል … ይኸውም እጣፈንታው በእጁ እንዳለ ወደ ማመን ፤ ብሎም ራሱን አምላክ አድርጎ ወደ ማሰብ ያደርሰዋል ፤ መጨረሻውም በእግዚአብሔር ላይ ማመፅ ይሆናል። ባንጻሩ የፈጣሪ ስጦታ የሆነውን ተፈጥሮን የሙጥኝ ያለ ማህበረሰብ እግዚአብሔርን ከፊት ማስቀደሙ ሳይታለም የተፈታ ነው … አርብቶ አደሮች … በተወሰነ ደረጃም አርሶ አደሮች እንደሚያደርጉት … ዝናበ ምህረቱን እንዲልክላቸው ጠብቆታቸው ከአምላካቸው ይሆናልና … በዚህም ደካማነታቸውንና ተጋላጭነታቸውን ይረዱበታል።

ለመሆኑስ መኪና ፤ ዘመናዊ ፎቴ ፤ ኮምፒዩተር ፤ ቲቪና ፤ መሰል የዘመናዊ ቴክኖሎጅ ቁሳቁሶች ስላሉን ስልጡን እንባላለን? … መሰልጠንስ ማለት ምን ማለት ነው? … በተክለ ሰውነታቸው እዚህ ግቡ የማይባሉ ፤ ድሆች ፤ ርሃብተኞች ፤ … ወ.ዘ.ተ ኋላቀር ይባላሉን? … እርግጥ ቴክኖሎጂ ሕይወትን ቀላል ያደርጋል … እንዲህስ ሲባል ሕይወት ቀለለ ማለት የግድ ተሰለጠነ ማለት ነውን? … በጭራሽ … እንዲያውም በተቃራኒው በእውነተኛ መንፈሳዊ ጥበብ ጥበበኛ የሆነ ፤ እርሱ ቁሳዊ ፍላጎቶቹን ትቶ በመንፈሳዊ አኗኗር የሚጠመድ ነው … ምድራዊ ግን በቁሳዊ ምቾት የሚያዝ ነው። … ታዲያስ እውነተኛው ጥበበኛ ማነው? … እውነተኛውስ ስልጡን የቱ ነው?

አንድ ማህበረሰብስ የሰለጠነ ይባል ዘንድ ድንጋይን በድንጋይ ላይ መካብ ይጠበቅበታልን? … በቁሳዊ ፍላጎት ታስሮ ለመልክና ለውበት ስለለፋስ ያደገ ያሰኘዋልን? … ባዶ ሆድስ የሚባለውን ያህል መጥፎ ነውን? … ድህነትስ እውን ጠላታችን ነውን? … ለኛ ለክርስቲያኖችስ ጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ ነው … ድህነት ደግሞ ተጋላጭነታችንን የሚያስታውሰን ባልንጀራችን … መጠጊያና ድጋፍ የሆነ አምላክ የሚያስፈልገን እንደሆንን የሚያሳየን መስታወታችን … ጓደኛችን ነው …

ደግሞስ ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለሀገሪቱ ድህነት ተጠያቂ ተደርጋ በየጊዜው ጣት ሲቀሰርባት ራሷን ለመከላከል መሞከር ይገባታልን? … በተቃራኒው ለሀገሪቱ እድገት አስተዋፅዖ እንዳበረከተች ለማሰመን መታተርስ ይኖርባታልን? … ድህነትስ ለእኛ ለልጆቿ መጥፎ ነገር ነውን? … በፍጹም! … እኛስ ምድራዊ ብዕልን ለመሰብሰብ ነፍሳችንን ወደ መሸጥ ስላልደረስን ፤ ድሆች ሆነን ፤ አንድ ጊዜ ለቅዱሳን በተሰጠችው በእውነተኛዋ እምነት ጸንተን በመኖራቸው እግዚአብሔርን እናመሰግናለን ፤ እንኮራለንም  … በግዝት በዓላቶቻችንም ወቅት ልናርስ አንወጣም … ክርስትና በመንፈስ ድሆች ለሆኑት እንጅ ፤ ምድራዊ ክብርንና ባለጸግነትን ፍለጋ አቅላቸውን እስኪስቱ ለሚደክሙት አይደለችምና።

አለማችን በሚያሳዝን መልኩ ከእውቀት የራቀ ፤ ውሳጣዊ ማስተዋልን የሚጠይቁ የመጠቁ ክሂሎችና ፤ ሃይማኖታዊ ፍሬዎች የሌሉት ፤ ለእኔ እና እኔ በሚል አስተሳሰብ የተሸበበ ፤ ጊዜ አጥፊ በሆኑ የቴክኖሎጅ መጫዎቻዎች ፤ ቪዲዮ ጌሞችና መኪናዎች ሱስ የተለከፈ ፤ እንዲህ ያለውንም አልባሌ ቁሳቁስ ለመግዛት በቀን እስከ 20+ ሰዓት የሚሰራ ፤ … ትውልድ በማፍራት ላይ ትገኛለች። … እንግዲህ ልብ እንበል … የሌት ተቀን ድካማችን እነዚህን የምዕራቡ አለም መታወቂያዎች የሆኑ የስልጣኔ መገለጫዎች ለመቅዳት/ለመኮረጅ መሆኑን እናስተውል። … የምዕራቡን አለም አስተሳሰብ … እንስሳዊ የስፖርት እንቅስቃሴዎቻቸውን… የሮክ ሙዚቃቸውን … ልቅ የወሲብ ፊልማቸውን … የሆሊውድን ባዕድ የህጻን አለም … ወ.ዘ.ተ … እንዲሁ ያለማመዛዘን … በጭፍን ለመገልበጥ … ምንኛ እንደምንለፋ እንገንዘብ።

ክርስትና … የሰውን ልጆች ከግለኝነት አስተሳሰብ አውጥቶ ራስን ወደ መካድ ፤ ለሌሎች ወደ መቆርቆር ፤ ለቤተክርስቲያን ወደ መቅናት ፤ አልፎ ተርፎም ለሀገር ወደ ማሰብ ያደርሳል ፤ ለአብነት በሀገራችን ኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች ብንሄድ ፤ የየትውልዱ ጥበባዊ የስልጣኔ ምስክሮች አቢያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ናቸው። ይኸውም በየዘመኑ የነበረው ትውልድ ነፍስና ስጋውን አስተባብሮ ፤ የነበረውን ግብዓት ሁሉ በመጠቀም ሊሰራ የሚተጋው ፤ እግዚአብሔር አምላኩ የሚከብርበትንና ደስ የሚሰኝበትን ስራ እንደነበረ እናስተውላለን። … ከዚህ አልፎ ተርፎም ነገስታቱ ምድራዊ ንግስናን በፈቃዳቸው ትተው በየገዳማቱ የምንኩስናን ሕይወት ለመኖር እንደገቡ ታሪክ ምስክር ነው።

እንዳለመታደል ሆኖ … እኛ ዛሬ … የየዕለት እንቅስቃሴያችን … ለዛ ወርቃማ የመካከለኛው ዘመን አእምሮ … ትርጉም አልባ በሆኑ ሰው ሰራሽ ማህበራዊ ችግሮች በሞሉበት ዘመን ተወልደናል። … በየዕለቱም በህሊናችን የሚመላለሱት ቁሳዊ ችግሮች … ይበልጡኑ ጠቃሚ የነበሩትን መንፈሳዊ ጉዳዮች እንዳናያቸውና እንዳናስባቸው ከልለውናል ፤ የዚህ የተጎዳ ትውልድ አባል መሆናችንም ፤ ራሳችንን ከአካባቢያችን ለይተን ፤ ከዚህ ማህበራዊ ጥፋትና ቁሳዊነት የምንጠበቅበትን መከላከያ ለማግኘት እጅጉን ከባድ አድርጎብናል። … እንዲህም ቢሆን ግን በትንሹ … አምላካችን እግዚአብሔር ፤ ለእኛ ለልጆቹ ያሰባትንና ያዘጋጃትን ፤ አባቶቻችንም የተመላለሱባትን ቀጥተኛ መንገድ ዕውቅና ልንሰጣት ግድ ይለናል … ይኸችውም ከውጫዊ ተፅዕኖ ነጻ የሆነችው … ለቁሳዊ ፍላጎት ቦታ የሌላትና ገዳማዊነትን የምትመስለው መንገድ ናት! … ይህንንም በመመስከር ደግሞ አናበቃም … ገዳማውያኑንና በበርሃ የወደቁትን አባቶቻችን መክሰስ እናቁም … ይልቁንም ጸሎታቸውንና መንፈሳዊ ምክራቸውን እንሻት … እንጠቀምባትም … ስለሚደርስባቸውም መረበሽና እንግልት ግድ ይኑረን … መሮጥ ያልቻለ ፤ ቢያንስ ለሚሮጥ ማጨብጭብ ይገባዋል እንዲል ብሂሉ።


በመጨረሻ የታሪክ ተመራማሪው ሮበርት ኮርኖክ የርዕሰ አድባራት አክሱም ፅዮንን ቄሰ ገበዝ ተጓሳቁለው በማየቱ ፤ የታላቋ ደብር ቄሰ ገበዝ ሆነው ሳለ ለምን እንዲያ ሊጎሳቆሉ እንደቻሉ በከፍተኛ መደነቅ ለጠየቃቸው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ በማቅረብ ጽሑፋችንን እናብቃ ፤ እንዲህ ነበር ያሉት ‘‘አምላክ ድሃ ያደረገን ለምክንያት ነው ፤ ይኸውም እንደተቀረው አለም ከፈቃዱና ከቅድስና መንገዱ እንዳንወጣ ነው’’



ወንድሞቻችን ሆይ ወደ መንፈሳዊ ጥበብ ወደ መንፈሳዊ ኃይል ወደ መንፈሳዊ ተዘምዶ እንዴት እንደጠራችሁ እወቁ … ‘ጥበቡ እንደ ሰሎሞን እንደ ሲራክ ያለ ነውእገሌ ጥበበኛ ነውያሉት እንደሆነመክሮ አስተምሮ ጠላቴን ያጠፋልኛል መንግስቴን ያጸናልኛልብሎ ይሻዋልእርሱ ግን ይህን ሳይሻ ወደ መንፈሳዊ ጥበብ እንደጠራችሁ ዕወቁ … ‘ኃይሉም እንደ ጌዴዎን እንደ ሶምሶን እንደ ዮፍታሔ ያለ ነውእገሌ ኃይለኛ ነውያሉት እንደሆነክንድ ይኾነኛል ጠላቴን ያደክምልኛልብሎ ይሻዋልእርሱ ግን ይህን ሳይሻ ወደ መንፈሳዊ ኃይል እንደጠራችሁ ዕወቁ … ‘ተዘምዶውም እንደ አብርሃም እንደ ኢዮብ ያለ ነውእገሌ ዘመዳም ነውያሉት እንደሆነጥግ ይኾነኛል አንድ በር ሁለት በር ይይዝልኛልብሎ ይሻዋልእርሱ ግን ይህን ሳይሻ ወደ መንፈሳዊ ተዘምዶ እንደጠራችሁ ዕወቁ …”
(1 ቆሮ 126 (ትርጓሜ))
“… እንግዲህብልህ ሰው በጥበቡ አይመካኃይለኛ በኃይሉ አይመካባለጸጋ በብልጽግናው አይመካየሚመካ ሰው በዚህ ይመካእግዚአብሔርን ዕወቁት ልብም አድርጉት …”
1 ሳሙ 29
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር።

ደጋፊ ምንባባት፦

  1.  “አሁንም አንች ቅምጥል ተዘልለሽ የምትቀመጭእኔ ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም …’ የምትይ ይህን ስሚ አሁን ግን በአንድ ቀን እነዚህ ሁለት ነገሮች በድንገት ይመጡብሻልኢሳ 478
  2.  “ከዝሆን ጥርስ በተሰራ አልጋ ላይ ለሚተኙ በምንጣፋቸው ደስ ለሚሰኙ ከበጎችም መንጋ ጠቦትን ከጋጥም ውስጥ ጥጃን ለሚመገቡ ከበገናው ድምፅ ጋር አስተባብረው ለሚያጨበጭቡ ሰዎች ይኸውም የማያልፍ ለሚመስላቸውበጽዋ የቀላ ወይን ለሚጠጡ እጅግ ባማረ ሽቱም ለሚቀቡ በዮሴፍ ስብራት ለማያስቡ ወዮላቸውአሞ 64
  3. ባለጠጋ ሰው ለራሱ ጠቢብ የሆነ ይመስለዋል አስተዋይ ድሃ ግን ይመረምረዋልተግ 411
  4. ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ የበጎችና የከብቶች መንጋዎች ነበሩኝብርንና ወርቅን ለራሴ ሰበሰብሁየወይን ጠጅ ጠማቂዎችንና አሳላፊዎችንም አበዛሁከሁሉ ይልቅ ከበርሁእነሆ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበርከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረምመክ 28
  5. ድሃውን ስለ ድህነቱ ይንቁት ዘንድ አይገባም ኃጢአተኛውንም ሰው ስለ ባለጸግነቱ ያከብሩት ዘንድ አይገባምሲራ 1023
  6.  “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አገልጋይ የለም ያለዚያ አንዱን ይወዳል ሁለተኛውንም ይጠላል ወይም ለአንዱ ይታዘዛል ለሁለተኛውም አይታዘዝም እንግዲህ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉምማቴ 624
  7. ሰው አለሙን ሁሉ ቢገዛ ነፍሱንም ቢያጣ ለሰው ምን ይረባዋል?” ማቴ 1626
  8.  “በእሾህም መካከል የወደቀው ቃሉን ሰምተው የባለጠግነት ዐሳብ የኑሮም መቆርቆር የተድላና የደስታ መጣፈጥም የሚያስጨንቃቸውና ፍሬ የማያፈሩ ናቸውሉቃ 814
  9. ስለምትበሉትና ስለምትጠጡት ለሰውነታችሁም ስለምትለብሱት አትጨነቁ ነፍስ ከምግብ ትበልጣለችና ሰውነትም ከልብስ ይበልጣልናሉቃ 1224
  10. እንደ ስጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁሮሜ  813
  11. እላችኋለሁ በመንፈስ ኑሩ እንጅ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ ሥጋ መንፈስ የማይሻውን ይሻልናየሥጋ ስራው ይታወቃል እርሱም ዝሙት ርኩሰት መዳራት ጣዖት ማምለክ ሥራይ ማድረግ መጣላት ኩራት የምንዝር ጌጥ ቅናት ቁጣ ጥርጥር ፉክክር ምቀኝነት መጋደል ስካር ይህንም የመሰለ ሁሉ ነውይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግስት አያይምገላ 516
  12. በእውነት ባልቴት የሆነች ብቻዋን የምትኖር ተስፋዋ እግዚአብሔር ነው ሌሊትና ቀንም በጸሎት ተፀምዳ ትኖራለች በጨዋታ ተድላ የምታደርግ ግን በሕይወቷ ሳለች የሞተች ናት” 1ጢሞ 55
  13. ነገር ግን በኋላ ዘመን ክፉ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ዕወቅ ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ገንዘብንም ሚወዱከእግዚአብሔር ይልቅ ተድላን የሚመርጡ  ይሆናሉ” 2ጢሞ 31
  14. ሙሴም በአደገ ጊዜ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እንቢ አለ ለጊዜውም በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠዕብ 1125
  15.  “ጻድቅ ሎጥም እያየና እየሰማ አብሯቸውም እየኖረ በክፉ ሥራቸው ከዕለት ወደ ዕለት ጻድቅት ነፍሱን ያስጨንቋት ነበር” 2ጵጥ 28

No comments:

Post a Comment