Pages

Thursday, September 26, 2013

ከዲ/ን ዳንኤል ክብረት ማለፊያ ቃለ መጠይቅ ፤ ሊታለፍ የማይገባው ነጥብ!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከዲ/ን ዳንኤል ክብረት ማለፊያ ቃለ መጠይቅ ፤ ሊታለፍ የማይገባው ነጥብ!!


እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!

ማስታወሻ፡-  ቀጥሎ የጻፍነውን የጻፍነው … እንደ እኛ አመለካከት … ክርስትናንም (በተለይም ኦርቶዶክስ ክርስትናን) እንደ መረዳታችን መጠን መሆኑን ልብ ማለት ይገባል፡፡ … ታዲያ ይሄ ምን ማስታወሻ ያስፈልገዋል? … ከሆነስ ግርጌ ላይ እንጅ እንዲህ ከራስጌ ምነው? ቢሉ … ያስፈልገዋል ነው መልሳችን … ዘመኑ ስለከፋ … በቀላሉ መረዳዳት ችግር ስለሆነ ፤ … ብዙ ሀተታ ሳናበዛ ወደ ጉዳያችን …

የቃለ መጠይቁ ማለፊያነት እንደምን ነው ቢሉ …

1 - በጽንፈኝነትና አክራሪነት መሃል ያለውን ልዩነት … ቢያንስ በጽንሰ ሀሳብ ደረጃ ያለውን ልዩነት በግልጽና በድፍረት ያስቀመጠ በመሆኑ፤

“… አንድን ነገር ወደ ጥግ ወይም ወደ መጨረሻው ጠርዝ ላይ መውሰድ ጽንፈኝነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ፣ አክራሪነት ይኹን ጽንፈኝነት በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብዙም ልዩነት ያላቸው ጉዳዮች አይደሉም፡፡ ልዩነታቸው በአፈጻጸም ላይ ነው፡፡ ጽንፈኞቹ ‹‹ይሄ እና ይሄ ብቻ›› የማለት ጠባይ አላቸው፡፡ አክራሪዎቹ ደግሞ ‹‹ይሄ እና ካልኾነ እንዲህ እናደርጋለን›› ወደሚልና ወደ ተግባሩ ርምጃ የሚያዘሙት ናቸው …”

2 - ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ ፤ አብረህ ተወቀጥ እንዲሉ ፤ የሌላትን ስም እየለጠፉባት የምትገኘዋ ቅድስት ቤተክርስቲያን ፤ ስሟን የሚያረክስ ክብሯን የሚያጎድፍ አስተምህሮ እንደሌላት በዝርዝርና በሚያኮራ ሁኔታ ያስቀመጠ በመሆኑ፤

“… ቤተ ክርስቲያን ለሌሎች ዕውቅና የመንፈግ ችግር አልነበረባትም፡፡ ዕውቅና ስትሰጥ ነው የኖረችው፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ አገሪቱ ሲመጡ፣ በወቅቱ የነበሩት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናን ባይቀበሉት ኖሮ ንጉሡ ብቻውን ምንም ሊያደርግ ባልቻለ ነበር ፤ … በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ግጭቶች ይፈጠሩ የነበሩት፣ ሌሎች ለእርሷ ዕውቅና መስጠት ሲያቅታቸው ነው፡፡ … በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ አክራሪነትን ሊያበቅል የሚችል መሬት አይገኝም …”

3 - ማህበረ ቅዱሳንን ለመምታትና ለማስመታት እየተደረገ ያለውን ሩጫ ምክንያት የለሽነት በሚገባ ያስገነዘበ በመሆኑ፤

“… ማኅበረ ቅዱሳን ግን እስከ አሁን ድረስ አክራሪ ኹኖ ያመጣው ነውጥ፣ ያሥነሳው ነገር፣ የደበደበው፣ የገደለው ሰው፣ ያቃጠለው ቤተ እምነት የለም …”

4 - ጎልቶ በሚሰማው የቃለ መጠይቁ ክፍል ላይ ፤ አክራሪ የሚለው መጥፎ ስም እየተለጠፈ ያለው በዋናነት ለማን ነው ለምንስ ትርፍ ሲባል ውጤቱስ ምን ይሆናል የሚሉትን ጉዳዮች በአጭርና በጠነከሩ ቃላት ግልፅ አድርጎ ያስቀመጠ በመሆኑ፤

ይህች ቤተ ክርስቲያን ተጠብቃ፣ ሥርዐቷን ይዛ ወደሚቀጥለው ትውልድና ዘመን መሻገር አለባት›› የሚሉትን አካላት ነው አሁን ‹‹አክራሪ›› ማለትና ዝም ማሰኘት የሚፈለገው፡፡ እነዚህን ሰዎች ዝም ማሰኘት ግን አይቻልም፡፡ ሃይማኖት የህልውና ጉዳይ ነው … የዚህችን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማንም በዕቅድ፣ በስትራተጂ፣ በምን ሊተምነው አይችልም፡፡ ታሪኳ የእግዚአብሔር ሥራ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹እገሌ ነው እርሷን የሚመራት›› ሊባል አይችልም፡፡ አስተዳደራዊ አመራር ይኖራታል እንጂ መንፈሳዊ አመራሯን ከፈጣሪ የምታገኝ ቤተ ክርስቲያን ናት …”

በእውነቱ ይበል የሚያሰኝ ነው … ዋናው ነገር ይሄ ነው! … አክራሪነት … "ሃይማኖታዊ መንግስትን ለማምጣት አላማ ባደረጉ ቡድኖች (አሸባሪዎች) የሚቀነቀን አፍራሽ አመለካከት ነው" ፤ የሚለው እሳቤ በመንግስት በኩል እንደ ሽፋን እየጠቀመ ያለ ማዘናጊያና መምቺያ ዱላ ነው ፤ … ሀቁ ግን ከዚህ በእጅጉ የራቀ ነው … መንፈሳዊ ተቋማቶቻችን የመንግስት ጉዳይ አስፈጻሚዎች ሊሆኑ አይገባም ፤ … የአስተዳደር እርከኖቻቸውም ምድራዊ ሀብትና ስልጣን ባሰከራቸውና ባረከሳቸው የመንግስት ቅጥረኞች/ጥቅመኞች ሊያዙ አይገባም ፤ … ዘላለማዊ መንግስትን እናገኝባቸዋለን ያልናቸው ፤ አባትና እናቶቻችን ብዙ ዋጋ የከፈሉባቸው አይነኬ መንፈሳዊ እሴቶቻችንና ስርዓቶቻችን ሊፈርሱ ፤ ሊጠፉና አያስፈልጉም ሊባሉ አይችሉም ፤ … እነዚህንና እነዚህን መሰል ጥያቄዎችን መጠየቅ ነው ፤ በመንግስት አክራሪነት ተብሎ የሚፈረጀው፡፡ መጽሐፍ … “ በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ስራህን አውቃለሁ … እንዲሁ ለብ ስላልህ ፤ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው” ራዕ 3፡-15 … ቢልም … ለብ ማለታችን የሚስማማው መንግስታችን ፤ አዚማችንን አስወግደን ትኩስ መሆን እንዳንችል ሊያኮላሸን ይፈልጋል … (ይህ ሲባል ታዲያ ሃይማኖታዊ መንግስትን ለማምጣት የሚጥሩ አካላት የሉም ብለን ለመሸምጠጥ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል ፤ አንገብጋቢ ስጋት አይደለም ለማለት እንጅ …)

የመንግስትን የአክራሪነት ትርጉም ከዚህ በበለጠ ሁኔታ መረዳት ይቻል ዘንድ የተወሰኑ ሀቆችን ልናሳያችሁ እንሞክር ፤ … በደሴ ከተማ ፤ የመስጅድ አስተዳዳሪዎች መንግስትን እንጅ እኛን አይወክሉም ፤ …  ሴት ልጅ ሳትከናነብ ብትሰግድ ችግር የለውም ፤ ማሰገድም ትችላለች ፤ የሚሉ እንግዳ ትምህርቶችን … ጥንት ያልነበሩ ስርዓቶችን ፤ … አመጡብን … በማለት መስጅዳቸውን ትተው በግለሰብ ቤት የሚሰግዱ ሙስሊሞች ፤ አክራሪዎች/አሸባሪዎች እየተባሉ ብዙ እንግልት እየደረሰባቸው ይገኛል ፤ ክርስቲያኖችም ቢሆኑ ፤ በእምነት ተቋማቶቻችን የአመራር ቦታዎች የሰገሰጋችኋቸው እንደራሴዎቻችሁ ፤ ቀናውን የአባቶቻችንን ስርዓት መናገር ትተዋልና እኛ ልንተወው አንችልም ፤ ቀዳሚት ሰንበትና ሰንበተ ክርስቲያን የምትባል ዕሁድን ያለነፍስ ስራ ሌላ አንሰራባቸውም ፤ ግዝቶች ናቸው … በእኒህ ቀናት … የፎረም በሉ የሊግ ስብሰባ አንመጣም … ስልጠና በሉ ሰልፍ አንወጣም ፤ … ያሉ … አክራሪና አሸባሪ ተብለው ስቃይ ያያሉ …

አሁን ባለፈው ሰሞን የመምህራን ጉባኤ ነበር ፤ የመንግስት ተወካይ በፕላዝማ ቀርበው ቃል በቃል ያሉትን እንንገራችሁ … ሰውየው ፤ ስለ ሃይማኖት አክራሪነት ጉዳይ ማብራሪያ/ምላሽ እያቀረቡ ናቸው … በንግግራቸው መሃል እንዲህ አሉ … … በኦርቶዶክስ ክርስቲያን በኩልም … መጽሐፍ ቅዱሳችን አንድ እምነት ፤ አንድ ጌታ ፤ አንድ  ጥምቀት ይላል በማለት ሌሎችን ለአመጽ የሚያነሳሳ የአክራሪነት አመለካከት የሚያንጸባርቁ ቡድኖች አሉ … እኔ እስከማውቀው ቁርዓንም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ልጆች በሰላም ተቻችለው የሚኖሩበትን እንጅ የሚጋጩበትን ትምህርት አያስተምሩም ፤ … እነዚህ ቡድኖች ምናልባትም ከተንሸዋረረው አመለካከታቸው አንጻር ተርጉመውት ሊሆን ይችላል … ይህ ግን የህገ መንግስቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል አስተሳሰብ ስለሆነ ሊታረም ይገባዋል፤” … ይህን ብለው እረፍት አደረጉ ፤ ውሃም ተጎንጭተው ቀጠሉ … “አንድ እምነት ፤ አንድ ጌታ ፤ አንድ  ጥምቀት የሚለው ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ቢኖር እንኳ ከህገ መንግስታችን ጋራ ስለማይስማማ … ለህገ መንግስታችን ህልውና አደጋ ስለሆነ ተግባራዊ ሊሆን አይገባም!” … ወደ ሌላ ድፍረታቸውም ተሻገሩ … “ከአሁን በኋላ የትኛውም የሃይማኖት ተቋም የሌላው ስህተት ነው ብሎ ማስተማር አይችልም ፤ ይህ የእኔ ብቻ ትክክል ነው የሚል አመለካከት ፤ ጸብ አጫሪ አመለካከት ነው (በሌላ አነጋገር የአክራሪነት አመለካከት ነው) …” ከዚህ በላይ ልንሰማቸው አልፈቀድንም (ልብ ያለው ልብ ይበል)

በአጠቃላይ ፤ ቃለ መጠይቁ ከላይ የተቀመጡትን ነጥቦች ጨምሮ ፤ በርካታ አስተማሪና መረጃ ሰጭ ሀሳቦች የቀረቡበት በመሆኑ ግሩም ቃለ መጠይቅ ነው ነው እንላለን ፤ እንዲህም ሆኖ …

ከቃለ መጠይቁ ሊታለፍ የማይገባው ነጥብ ደግሞ …

መገንዘብ/መገናዘብ ተብሎ የቀረበው ነው፡፡
“… አንድን ሙስሊም ‹‹እንኳን ለመውሊድ በዓል አደረሰኽ›› ስትለው ተገንዝበኸዋል ማለት ነው፡፡ በዚያ በዓል ላይ ተስማምተኸ ላይኾን ይችላል፡፡ እንደውም ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያ ብዙኀን መገናኛዎች ለሙስሊሞች ‹‹እንኳን ለዒድ አል አረፋ በዓል አደረሳችኹ›› ለክርስቲያኖች ‹‹እንኳን ለጥምቀት በዓል አደረሳችኹ›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ግን ለምንድን ነው እንዲህ የሚሉት? እኔ በኢትዮጵያዊነቴ የሙስሊም ወገኔን በዓል ገዝቼዋለኹ፡፡ ሙስሊሙም የእኔን በዓል ገዝቶታል፡፡ እርሱም በእኔ እምነት እድናለኹ፤ እኔም በእርሱ እምነት እድናለኹ፤ አላልንም እንጂ በባህላችን አንዳችን የሌላችንን በዓል ገንዘብ አድርገነዋል፡፡
ስለዚህ በብዙኀን መገናኛ በኩል መባል የሚኖርበት ‹‹ለኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለዒድ አል አረፋ፤ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በዓል አደረሳችኁ›› ነው፡፡ ሚዲያው ይለየናል? እኛ ያልተያየነውን ለምን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚለያየን እላለኹ፡፡ ብዙውን ጊዜ እኔ ጓደኛዬን ‹‹እንኳን አደረሰን›› ነው የምለው፡፡ ለምሳሌ እርሱ የመውሊድን በዓል ሲያከብር የሚያገኘው ሃይማኖታዊ በረከት እንዳለ አስቦ ነው፤ ልክ እኔ ጥምቀት በማከብርበት ጊዜ እንደማደርገው፤ ግን እርሱን እንኳን አደረሰኽ ስለው እርሱ በዓሉን ሰላማዊ ኾኖ፣ ነጻ ኾኖ፣ ደስ ብሎት የሚያከበርበትን ከባቢያዊ ኹኔታ መፍጠር ግዴታዬ ነው…”
ባንሳሳት … መውሊድ ‹ኢየሱስ ነቢይ እንጂ አምላክ አይደለም›  ‹አምላክ አይወርድም አይወለድም› ብሎ የሰበከ የ‹ነቢዩ› መሐመድ የልደት በአል ነው፡፡ … ታዲያ … አንድ ሃይማኖቱን በአግባቡ የሚያውቅና ለእምነቱ የሚቆረቆር ክርስቲያን … በሞቱ ሕይወት የሰጠውን የክርስቶስን አምላክነት ክዶ ላስካደ ‹ነቢይ› ልደት ‹እንኳን አደረሳችሁ›፣ እንዴት ሊል ይቻለዋል? … ‹እንኳን አደረሰን›ስ ጤናማነቱ ወዴት ነው ፣ … መንግስት … የሃይማኖታችን ህልውና መሰረት ክርስቶስ ነው ማለትን አስትቶ ፤ በአደባባይ ህገ መንግስታችን የሃይማኖታችን ህልውና መሰረት እያስባለው ፤ … የኢትዮጵያን የቅድስት ድንግል ማርያም የአስራት ሀገርነት አልሰማህም እያለው ፤ … መጽሐፍ ቅዱሱንም ቢሆን ከህገ መንግስቱ ጋራ እስካልተጋጨ ድረስ ነው ልትመራበት የምትችለው እያለው ፤ … ከሁሉ አስቀድሞ ኢትዮጵያዊ ነህ … ከዛ ቀጥለህ ነው የምታምነውን የምታምነው እያለው ፤ … በምን ሂሳብ “የመውሊድን በዓል በኢትዮጵያዊነቴ ‹ገዝቼዋለሁ›፤ ገንዘቤ አድርጌዋለሁ” ለማለት ይደፍራል? … እንዲህ ከክርስትናው ጋራ በውል ያልተስማማ ኢትዮጵያዊነትስ ለእርሱ ምኑ ነው?
ወንጌልና የአባቶቻችን ትውፊት የሚያስተምረን ፤ አንድ ክርስቲያን ከምንም ነገር አስቀድሞ ክርስቲያን መሆኑን ነው ፤ የአገር ተወላጅነት (ኢትዮጵያዊነት) ወይም ማንኛውም ሌላ ዓይነት እሴት ዋጋ ሊኖረው የሚችለው ከክርስትናው ጋር ከሚፈጥረው ዝምድና አንጻር ብቻና ብቻ ነው ፤ … እንዲያ ባይሆን ኖሮ ፤ ሀገራችን በሰማይ እንደሆነ ያስተማሩ ፤ እነ ቅዱስ ጳውሎስ ክርስትናቸውን ከይሁዲነታቸው አስበልጠው ሁሉን ትተው ባልተሰደዱ ነበር  ፤ ተስአቱ ቅዱሳንም ሮም መከራ ባጸናችባቸው ጊዜ ሀገራቸውን ጥለው በባሕልም በቋንቋም ወደማይመስላቸው ወደ ኢትዮጵያ ባልፈለሱም ነበር ፤ … በአጭሩ ፤ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ እንጂ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ሊኖር አይችልም ፤ አስቀድሞ ክርስቲያን ከዚያ ደግሞ በትውልድ ስፍራው ኢትዮጵያዊ … በአጠቃላይ … ክርስትና ላይ ያልተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት ክርስትናን ወደ መካድ ማድረሱ አይቀሬ መሆኑ ሊስተዋል ይገባል፡፡

በሃይማኖት ዋጋ ፤ ባሕልን ዘርንና አብሮ መኖርን ለመግዛት ፤ ለማጠንከርና የማንነት መሰረቶች ለማድረግ መንቀሳቀስ ፤ መጨረሻው የክርስትናን ፋይዳ ከህልውና አስኳልነት ወደ ኮስሜቲክ ማጊያጌጫነት ወደ ማኮሰስ ያደርሳል፡፡ አንድን ሙስሊም መውሊድን ሲያከብር ‹እንኳን አደረሰን› ባልን በዚያች ቅጽበት ‹ነቢይ› የሚለውን የሙሐመድን የልደት በአል የተለየና ፤ የከበረ መሆኑን እየመሰከርን ነው ፤ ይህንን ስንናገርም ‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ አይደለም› ላለው ለሙሐመድና ፤ ለመሰረተው የተሳሳተ ትምህርት በተዘዋዋሪ እውቅና መስጠታችን ይሆናል፡፡ ለመሆኑስ … የጥንት ክርስቲያኖች ፤ ጣዖት አምላኪዎችና አረማውያን ፤ በዓላቶቻቸውን ሲያከብሩ ፤ … የእንኳን አደረሰን ቀልድ ይቅርና ‹እንኳን አደረሳችሁ› ይሏቸው የነበረበት ዘመን ስለመኖሩ ምን ዓይነት ታሪካዊ ማስረጃ ይገኛል?


“ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደመጣ (ወልድ እንደወረደ እንደተወለደ) የማያምን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም”
1ዮሐ 4:-3





እርግጥ … ሙስሊሞች በሃይማኖት ባይመስሉንም እንኳ ፤ በጌታችን ከተሰበከልን የፍቅር ሕግ የተነሳ … መልካሙን ሁሉ ልንመኝላቸው አግባብ ነው ፤ ነገር ግን ግለሰቡን እንደሰውነቱ በመውደድና ፤ ለቆመለት ሃይማኖት እውቅና በመስጠት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ መልካሙን ለሁሉ መመኘት አንድ ነገር ሆኖ መውሊድን ሲያከብር ‹እንኳን አደረሰህ!› ማለት ከዚያም አልፎ ‹በኢትዮጵያዊነቴ የሙስሊም ወገኔን በዓል ገዝቼዋለሁ› ወደ ማለትና ብሎም ‹እንኳን አደረሰን› እስከማለት ፤ እንዲሁም “ደስ ብሏቸው የሚያከብሩበትን ‹አከባቢያዊ ኹኔታ (እስከ) መፍጠር› (እዚህ ላይ አገላለጹ መልካሙን ከመመኘት ባለፈ በዓሉ እንዲከበር ሱታፌ ማድረግን እንደሚያመለክት ልብ ይሏል) የሚደርስ ከሆነ ፤ መሰረታችን ክርስትና ይሁን አይሁን ጥያቄ የሚያስነሳ ነው ፤ ፍጻሜውም ክርስቲያናዊ ማንነትን ማጣት ይሆናል፡፡ …

በአጠቃላይ … ‹‹እርሱም በእኔ እምነት እድናለኹ፤ እኔም በእርሱ እምነት እድናለኹ፤ አላልንም እንጂ በባህላችን አንዳችን የሌላችንን በዓል ገንዘብ አድርገነዋል›› የሚለው ገለጻ በራሱ እንደማሕበረሰብ በዘመን አመጣሹ የመቻቻል/የመገናዘብ ርዕዮት ምን ያህል እንደተወሰድን የሚያሳይ ነው፡፡ …

ዘመኑ ወገንተኝነታችንን ግልጽ አድርገን የምናሳይበት ዘመን ነው ፤ … ወይ እዚህ አልያም እዚያ መሆንን ግድ የሚል ዘመን … በክርስትና ደግሞ ጥንቱንም በመሃል ብሎ ነገር የለም … በራድ አልያም ትኩስ … ለብ ማለት ዋጋ የለውም!! … መጽሐፍ … አንድ ጌታ ፤ አንድ እምነት ፤ አንድ ጥምቀት በማለት ያውጃል … አበውም የቀናችቱን መንገድ እንድንከተላት መክረውናል … ጌታችንም በምድር ለመሰከረለት ሁሉ በሰማይ አባቱ ዘንድ እንደሚመሰክርለት ኪዳን ሰጥቷል … ስለሆነም … አንድ መንገድ ብቻ አትበሉ የሚሉንን ልንሰማቸው አይገባንም … ወደቀናችው መንገድ ላልተመለሱትም ፤ የሚጓዙበት ጎዳና የጥፋት እንደሆነ ልንመክር ፤ የክርስቶስንም የማዳን ስራ ልንመሰክር ፤ ጣዕሙን ፍቅሩን እንዲቀምሱት ልንጋብዝ ግድ ይለናል፡፡ … መንግስት … ምድራዊ ስልጣኔን ይነቀንቃል ብሎ የሚሰጋበትን ጉዳይ ፤ እገነባታለሁ የሚላትን አዲሲቷንና ፤ ዘመናዊቷን ኢትዮጵያ በመገንባት ሂደትም መሰናክል ይሆነኛል ያለውን ሁሉ ፤ ከፊቱ ማስወገዱ የሚጠበቅ ነው ፤ … ከስጋ ድሎት ፤ የነፍስን እረፍት ፤ ከ60 እና 80 ዓመታት ምድራዊነት ፤ ዘላለማዊ ሰማያዊነትን ያስበለጠ ክርስቲያንም ባንጻሩ ፤ ተስፋ የሚያደርገውን ዘላለማዊ ርስት ሊያሳጣው የሚችልን ማንኛውም ተግዳሮት ታግሎ ማሸነፍ ይኖርበታል፡፡ … ትንሽ ለምድራዊው መንግስት ፤ ትንሽ ደግሞ ለሰማያዊው … የሚለው አካሄድ ፤ ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ ለመውጣት እንደመፈለግ ነው ፤ … መጽሐፍ ግን ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም ይለናል፡፡


“ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው አገልጋይ የለም ያለዚያ አንዱን ይወዳል ሁለተኛውንም ይጠላል ወይም ለአንዱ ይታዘዛል ለሁለተኛውም አይታዘዝም” 
ማቴ 6፦24






ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ!!

በዓሉን የሰላም በዓል ያድርግልን፡፡


ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤



  

No comments:

Post a Comment