Pages

Monday, May 11, 2015

እውነቱን እውነት ፤ ሀሰቱንም ሀሰት ማለት ይገባል!! መቻቻልና መገናዘብም ፤ መበራረዝና መቀላቀል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡



በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
እውነቱን እውነት ፤ ሀሰቱንም ሀሰት ማለት ይገባል!!

መቻቻልና መገናዘብም ፤ መበራረዝና መቀላቀል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡


ጤና ይስጥልን …


ይህችን አጭር ማስታወሻ (አስተያየት) ለመጻፍ ያነሳሳን ጉዳይ …. ከሰሞኑ ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን በክርስቲያን ወንድሞቻችን ላይ የተፈጸመውን አረመኔያዊ የግድያ ተግባር ተከትሎ ፤ በሰማዕታቱ ማንነት ላይ (ይልቁንም … ቀድሞ “ጀማል” ፤ አዲስ በተገኘው መረጃ ደግሞ “ኤፍሬም” ስለተባለ ወገናችን ማንነት) ፤ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ ያየነው ቅጥ ያጣ የሃሳብ (የአመለካከት) ልዩነት (ሽኩቻ) … ነው፡፡ … የቀደመው ወይንስ አዲሱ መረጃ ይሻላል የሚለው ጉንጭ አልፋ ክርክር ብዙም ሊባልበት የሚችል ባይሆንም ቅሉ ፤ በተያያዥነት ያየናቸው ሊታለፉ የማይገባቸው ጉዶዮች አሉና ፤ የመረጃውን ጉዳይ እንደ መንደርደሪያ አድርገን ወደ ጉዳያችን እንዘልቃለን፡፡


ከሁሉ በፊት … በሃይማኖታቸው ምክንያት ሰማዕትነት የተቀበሉትን ወንድሞቻችንን አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱሳንን ባከበረበት ክብር ያከብራቸው ፤ ለቅዱሳን ሰማዕታትም ያቀዳጃቸውን የክብር አክሊል ያቀዳጃቸው ፤ ቤተሰቦቻቸውንና ወዳጆቻቸውን ያጽናናቸው ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን፡፡


ይህ አሰቃቂ መርዶ ከተሰማባት ከዚያች ክፉ ዕለት እንጀምር … ዜናውን የያዘው የምስል ወድምፅ ውጤት ከአሸባሪ ቡድኑ መለቀቁን ተከትሎ የተለያዩ የዜና አውታሮች ወሬውን እየዘግቡትና … የተለያዩ የውጭ መንግስታትም በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ጭካኔ እያወገዙ ባሉበት ሰዓት … መንግስታችን … “የድርጊቱ ሰለባዎች ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውንግብፅ የሚገኘው ኢምባሲ አላረጋገጠም ፣ በርግጥ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ለማረጋገጥ እየጣርን ነው” … ማለቱን ሰምተን ፤ ብዙዎቻችን … “የሟቾቹን አስከሬን አግኝቶ ማረጋገጥ በማይቻልበት ሁኔታ … ምን ነካቸው? … ደግሞስ እኛ የወገኖቻችንን መልክና የፊት ገፅታ አጣነውን? … ቢሳሳቱስ … “ወገኖቻችን ታረዱ” ብለው በማዘናቸውና በመቆጨታቸው … የሚያባጭባቸው ማን ሊኖር?” … የሚሉና ፤ መሰል መሪር ሀዘን ወለድ ሃሳቦችን … መለዋወጣችን ይታወቃል፡፡


ከላይ መንግስትን በወቀስንበት አመክንዮ መሰረትነት … በወንድማችን ኤፍሬም ማንነት ላይ እየተንጸባረቀ ያለውን ልዩነት ለመረዳት እንሞክር ፤ … መንግስት ዜናውን ከሰማበት ቅጽበት አንስቶ መሠዋታቸውን እውቅና ቢሰጠውና አስከትሎም ተገቢ የሚባሉ እርምጃዎችን ቢወስድ ፤ ከዛም የድርጊቱ ገፈት ቀማሾች ኢትዮጵያውያን አለመሆናቸው ቢረጋገጥ ምን ይከሰት ነበር? … እንደ ብዙዎቻችን እምነት … ምንም … እንዲያውም መንግስት ለሕዝብ ያለውን ወገንተኝነት ያሳየበት ክስተት ሆኖ ያልፋል … ወዲህ ደግሞ እንመለስ … አስቀድሞ  “ጀማልየተባለ ሙስሊም ወንድማችን በሊቢያ ከተሠዉ ክርስቲያኖች ጋር አብሮ ተሠዉቷል” ተባለ … ይህምየኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ፍቅር ማሳያ” ተደርጎ ተወሰደ …  በ “‹ጀማል› አምሳልም አንዱ ለሌላው ያለውን ተቆርቋሪነት አየን” አልን … ሁሉም ጥሩ ነው … አንዳችም ችግር የለበትም … በቅርቡ ደግሞ ፤ “የተለያዩ ሁኔታዎች የፈጠሩት የመረጃ ክፍተት እንጅ … ‹ጀማልነው ተብሎ ሲነገርለት የነበረው ወንድማችንኤፍሬም የተባለ ኤርትራዊ ፤ ቃኘው ሠፈር ይኖር የነበረ ክርስቲያን ነው” የሚል አዲስ መረጃ መጣ … ቀጥሎ ሊሆን የሚገባው ነገር የመረጃውን ትክክለኝነት ማጣራት ነው ፤ … ይህ ከሆነ በሁዋላ ታዲያ ፤ የቀደመውን እንደተቀበልን ሁሉ ይህንን የማንቀበልበት ምን ምክንያት ይኖራል? … በምን ሒሳብ አዲሱ መረጃ (እውነቱ) የቀደመ ፍቅራችንን የሚቀማን ተደርጎ ይቆጠራል? … እንደምንስ እንደ አንድ ሀገር ሕዝብነት ያስተሳሰረንን ገመድ እንደሚያላላ ተደርጎ ይወሰዳል? … እንዲህ ከሆነስ ታዲያ ፤ ከላይ መንግስት ቢሳሳት

እን ወገንተኛነቱን አሳየ እንጅ ሌላ ነገር የለውም (ምንም አይባልም) ፤ ስንል የነበረው ነገር እርግጥ እንዲያ አድርጎ ተሳስቶ ቢሆን ኖሮ አይሰራም ነበር ማለት ነው?



የቀድሞውን … የሀሰት ማንነትና ታሪክ የሚሹ ወገኖች ለዚህ ፍላጎታቸው የተለያዩ ምክንያቶችን እንደሚያቀርቡ ሁሉ ፤ በሌላ በኩል የአዲሱን (የትክክለኛውን) መረጃ መነገርንም የሚደግፉት እንደ አመክንዮ የተለያዩ ምክንያቶችን ያመጣሉ (ከቤተሰቡ ፤ ከቤተክርስቲያን ፤ …. አንጻር) … እውነት ለመናገር ግን የአንድን መረጃ ጠቀሜታ አልያም ጉዳት መተንተን የሚቻለው የመረጃውን ምንነት ካወቁ በሁዋላ ነው … ስለሆነም በኛ አመለካከት መረጃው መነገር የሚኖርበት እውነት ስለሆነ ብቻና ብቻ ነው! … ከዚያ በ|ላ ቋሚ ብዙ ያወራልና … ነገርን እንደ መረዳታችን መጠን … እንደ እምነታችን … እንደ አመለካከታችን … እንደ |ላ ታሪካችን … እንደምንከተለው ርዕዮት … የፈለጋችሁትን ስም ልትሰጡት ትችላላችሁ … እንደፈለግን ልንተረጉመውና ልንበልተው እንችላለን፡፡ … በድጋሚ ግን እነ እንቶኔም ደስ እንዲላቸው … እነንትናም እንዳይከፋቸው ሳይሆን … እውነት ስለሆነ ብቻ እውነቱ መነገር ይኖርበታል፡፡


ለአብነት … ይህንኑ የሀሳብ ልውውጥ አስመልክቶ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ፤ የአዲሱን (የትክክለኛውን) መረጃ ይፋ መሆን በመቃወም … “ለሰብዓዊነት የተከፈለን መስዋዕትነት ዝቅ አድርጎ ለሃይማኖት የተከፈለ አድርጎ አቀረበብኝ” ማለታቸውን እናንሳ … አመለካከታቸውን እናከብራለን … ምቅዋማቸው (እምነታቸው) እንዲያ ነው ማለት ነው … ለእርሳቸው … ለሰብዓዊነት የተከፈለ መስዋዕትነት ለሃይማኖት ከሚከፈል መስዋዕትነት ይበልጣል … ያም ሆኖ እውነቱ … የልጆቹ መስዋዕትነት … ለሃይማኖት የተከፈለ መስዋዕትነት መሆኑ ነው … አሸባሪው ቡድን ፤ ለዓለም ሕዝብ ከማስፈራሪያ ቃላት ጋር ባስተላለፈው የምስል ወድምፅ መልዕክቱ … በግልፅ የጠላታችን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አባላት በማለት ተናግራል … ግዳዮቹን … የእስልምና እምነትን ስለማመናቸውና ስላለማመናቸው የቁርዓን ጥያቄ እየጠየቀ የሚገድልን ቡድን እያዩ … ሌላ የሌለን ነገር ለመፍጠር … የሌለን ስም ለመስጠት መሞከር ተገቢ አይመስለንም … ከሰማዕታቱ የእምነት ጽናት ፤ ከመታመናቸው ልክ መማር ባይቻል ፤ አድንቆትን መቸር ፤ እርሱም ባይቻል እውነትን እንደወረደ መቀበል ግን ለማንም አይከብድምና ፤ … ደግሞም የክርስቲያን እምነት ተከታዮች ለእምነት ታምኖ መስዋዕት መሆን በሌላ እምነት ተከታዮች የሚያመጣው አንዳች ችግርም የለም ፤ ተከባብሮ የመኖር የቆየ በጎ ልማድንም የሚጋፋበት ሁኔታ የለም … 


እርግጥ በዚህ ዘመን (በዘመነ ሉላዊነት) የእምነት ዋጋዋ እያነሰ ሁሉም ነገር በሰብዓዊነት መጋረጃ ውስጥ እየተጠቀለለ መምጣቱ እየታየ ያለ እና የማይካድ ሀቅ ነው ፤ ዘመኑም ፍጻሜ ዘመን ነውና ይህ ሊሆን ግድ ነው … እናም ክርስቲያን ለሆነ ሁሉ … ይልቁንም ለእኛ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች የሚደንቅ አይሆንም ፤ … ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስከ አለም አቢያተ ክርስቲያናት ህብረት ያሉ ታላላቅ ተቋማት በሰው ልጆች መካከል ያሉ ማናቸውንም ልዩነቶች ለማጥፋትና አንድ ዓለምን ለመመስረት ፤ ግልጥና ስውር እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ ፤ ያም ቢሆን ፤ አስተዋይና አመዛዛኝ አእምሮ እንዲሁም ያሻውን የሚመርጥበት ነጻ ፈቃድ ከፈጣሪው የተቸረ የሰው ልጅ እንደሚመርጠው የሕይወት ጎዳና መለያየት ፤ የሕይወት አቅጣጫውም እንደሚለያይ አይጠረጠርም፡፡ የልዩነታችን እውነታ እንዳለ ሆኖ ታዲያ ፤ በተለይ በሀገራችን በኢትዮጵያ አሁን አሁን ፤ እኛ ኦርቶዶክሳውያን ከሌሎች የእምነት ተከታይ ወገኖቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ፤ አንድነታችንን ፤ መተሳሰባችንን ፤ መከባበርና መገናዘባችንን የምናሳይበት መንገድ ሊጤን የሚገባው ነው ፤ … “እግዚአብሔር በስጋ መገለጡን (መውረድ መወለዱን) የማያምን ከእግዚአብሔር ዘንድ አይደለም” እንዲል መጽሐፍ …


ወንጌልና የአባቶቻችን ትውፊት የሚያስተምረን ፤ አንድ ክርስቲያን ከምንም ነገር አስቀድሞ ክርስቲያን መሆኑን ነው ፤ የአገር ተወላጅነት (ኢትዮጵያዊነት) ወይም ማንኛውም ሌላ ዓይነት እሴት ዋጋ ሊኖረው የሚችለው ከክርስትናችን ጋር ከሚፈጥረው ዝምድና አንጻር ብቻና ብቻ ነው ፤ … እንዲያ ባይሆን ኖሮ ፤ ሀገራችን በሰማይ እንደሆነ ያስተማሩ ፤ እነ ቅዱስ ጳውሎስ ክርስትናቸውን ከይሁዲነታቸው አስበልጠው ሁሉን ትተው ባልተሰደዱ ነበር  ፤ ተስአቱ ቅዱሳንም ሮም መከራ ባጸናችባቸው ጊዜ ሀገራቸውን ጥለው በባሕልም በቋንቋም ወደማትመስላቸው ወደ ኢትዮጵያ ባልፈለሱም ነበር ፤ … በአጭሩ ፤ ክርስቲያን ኢትዮጵያዊ እንጂ ኢትዮጵያዊ ክርስቲያን ሊኖር አይችልም ፤ አስቀድሞ ክርስቲያን ከዚያ ደግሞ በትውልድ ስፍራው ኢትዮጵያዊ … በአጠቃላይ … ክርስትና ላይ ያልተመሰረተ ኢትዮጵያዊነት ክርስትናን ወደ መካድ ማድረሱ አይቀሬ መሆኑ ሊስተዋል ይገባል፡፡ በአጭሩ በሃይማኖት ዋጋ ፤ ባሕልን ዘርንና አብሮ መኖርን ለመግዛት ፤ ለማጠንከርና የማንነት መሰረቶች ለማድረግ መንቀሳቀስ ፤ መጨረሻው የክርስትናን ፋይዳ ከህልውና አስኳልነት ወደ ኮስሜቲክ ማጊያጌጫነት ወደ ማኮሰስ ያደርሳል፡፡

ለምሳሌ … የቀድሞው የሀሰት መረጃ አያስፈልግም ከሚሉት ወገን የሆነ … “ፍቅራችንን በውሸት ሃውልት ላይ አናቆምም!!” … በሚል ርዕስ … በአካል ንጉሴ በተባሉ ሰው የተጻፈን አጭር ጽሑፍ ፤ የተወሰነ ክፍል እናሳያችሁ … ጽሑፉ ስለመቻቻል እያብራራ ነው … “የኛ ግን ከዚህ ይለያል” (የእኛን መቻቻል ማለታቸው ነው) “ሰዎች እዚህ እኮ /ወሎ ማለቴ ነው/ “አይ ይህ ሃይማኖት አልከፈለኝም (አላዋጣኝም ማለታቸው ነው)  ቀይሬ ልሞክረውብሎ የሌላኛው ሰው ቤተ እምነት ውስጥ የምታገኙት ሚስቴ እምነቷ ሌላ ነው የኔ ደግሞ ወዲህ ነው፡፡የሚል ጋሽ ስብሃት እንዳለውእግዚአብሔር ይመስገን መስጊድ ተሰራልን አልሃምዱሊላሂቦታችን በሰላም ገባየሚል ሉላዊነት ቀድሞ የገባው የዋህ የፍቅር ሰው ነው የማህበረሰቡን አስተሳሰብ ያነጸው … እኔ ግን አምናለሁ ፤ በኛ ዘንድ መቻቻል ሳይሆን ህይወት አለ - በቃ ኑሮ ነዋ እኛ ያለው፡፡ ለታቦት ስለት የሚያገባ ሙስሊም የሸሆችን በር የሚያንኳኳ ክርስቲያን መቻቻል ምናምን ብሎ ቃል ወይም የውሸት የፍቅር ሃውልት አያስፈልገውም” በማለት ይቀጥላሉ … እዚህ ላይ ታዲያ የጽሑፉን ሃሳብ ባናምንበትም የጸሐፊውን እምነት እንደምናከብር እንግለፅና ወደ ጉዳያችን እንመለስ … ትልቁ ነጥብ እዚህ ላይ ነው … ጸሐፊው መሬት ላይ (በሕዝቡ) መካከል ያለውን ነገር ከመቻቻል በላይ የጠነከረና እንዲያውም ሕይወት እንደሆነ ይሞግታሉ … እንደኛ አረዳድ (አመለካከት) ግን ፤ ይህ መቻቻል (መገናዘብ) አይደለም … ይህ ክርስቲያን ለሆነ ሁሉ ጥፋት እንጅ ሕይወት አይሆንም … ባጭሩ ስም ሊወጣለት ካስፈለገ … ስሙ መቀላቀል ነው … አልያም መበራረዝ … እንደሚገባንም መቀላቀል(መበራረዝ) ለማናችንም አይጠቅምም …

ስለሆነም እኛ ክርስቲያኖች ይህን መሰሉን አመለካከት ልናስተካክል ይገባል እንላለን … 60 እና 80 ዘመን በምንቆይበት ምድራዊ ሕይወታችን ስለሚሆነው አብሮ የመኖር ነገር ከመጠን ባለፈ በመጨነቅ ፤ ተስፋ የምናደርገውን ዘላለማዊ ሕይወት እንዳናጣ ፤ ሁሉን ነገር በልክ መያዝ ያስፈልጋል ፤ አብሮ መኖርን ፤ መከባበርን ፤ መተሳሰብን ፤ መገናዘብን ስናስብ ፤ …. በእግዚአብሔር በአምላካችን ፊት እንዴት እየተመላለስን እንደሆነ … ትዕዛዛቱ (ህግጋቱ) ለመንገዳችን መብራት ሆኖ እየመራን ስለመሆኑ … የቤቱ (የቤተክርስቲያን) ስርዓት ምን እንደሚል … ከሌሎች የእምነት ተከታይ ቤተሰቦቻችን ፤ ጎረቤቶቻችን ፤ የስራ ባልደረቦቻችን ፤ … ጋር ያለን ግንኙነት ፈጣሪ በሚወደው መልኩ ስለመሆኑ በተዳኝ በጥልቀት ማሰብ ይኖርብናል፡፡

በመጨረሻ … እንዲህ ማለታችንን  የጠብ አጫሪነት አድርጎ የሚወስድ አንባቢ አይጠፋምና ማሳሰቢያ ቢጤ ብናክል አይከፋምና እነሆ ፤ … የተከበራችሁ አንባብያን ሆይ … ሃሳባችን ባጭሩ … ቅድሚያ ለሚገባው ቅድሚያ መስጠትን ከሰማዕታቱ እንማር ነው! … መጻተኞች በሆንባት በዚህች ምድር ከሚሆነው ነገር በላይ ለእኛ ለክርስቲያኖች ሊያሳስበን የሚገባ የዘላለማዊ መንግስት ጉዳይ አለብን ነው! ፤ እንጅስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም እንድንኖር የአምላካችን ፈቃድ ይህች ናት … በሌሎች የእምነት ተከታዮች ላይ የማይገባ ጥላቻን ስለማብቀል አይደለም ፤ በተቋሞቻቸውም ላይ ግፍን ስለመፈጸምም አይደለም … ክርስትና እንዲህ ያለውን ድርጊት አያስተምርምና … እንዲያውም የክርስቲያኖችን ሕይወት የቀጠፉት ሰዎች እንኳ ድርጊታቸው የሚወገዝ ቢሆንም ቅሉ እንዲያ ያደረጉት በክፉ መንፈስ እየተመሩ በመሆኑ ፤ ልቦና እንዲሰጣቸው ምህረትንም እንዲያገኙ ከእግዚአብሔር መለመንን የሚያስተምር ነው … ክርስትና!

በቀረውስ … እውነቱን እውነት ሀሰቱንም ሀሰት ማለት ይገባል!!

ቸር ያቆዬን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡



No comments:

Post a Comment